ኢራን ሴት ተማሪዎችን “ሆን ብለው” የመረዙ አካላት በሞት እንደሚቀጡ ገለጸች
የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ፥ ሴቶች ተማሪዎች ላይ ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት እንዲጣራ አሳስበዋል
በኢራን ሴቶች እንዳይማሩ የሚፈልጉ አካላት ከ1 ሺህ በላይ ሴት ተማሪዎችን በኬሚካል መመረዛቸው ተነግሯል
በኢራን ሴት ተማሪዎችን በኬሚካል የመረዙ አካላት ይቅር እንደማይባሉ የሀገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ተናገሩ።
ድርጊቱን ሆን ተብሎ የተፈጸመ ከሆነም ወንጀለኞቹ እስከሞት የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ነው ያሉት።
ባለፉት ሶስት ወራት ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ባስተናገደችው ሀገር፥ ከ1 ሺህ በላይ ሴት ተማሪዎች በኬሚካል መመረዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የመመረዝ አደጋው የሞት አደጋን ባያስከትልም በርካታ ሴቶች የመተንፈሻ አካላት ችግርና ተያያዥ ህመሞች እንዳስተናገዱ ነው የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ያነሱት።
ከቆም ከተማ የጀመረው የመመረዝ አደጋ ከኢራን 31 ግዛቶች 25ቱን አዳርሶ በርካታ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እስከማቆም መድረሳቸው ይታወሳል።
ለተማሪዎቹ መመረዝ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የማይፈለጉ አካላት ተጠያቂ ተደርገዋል።
ለዚህም ከአንድ የወንዶች ትምህርት ቤቶች ውጭ ሁሉም የጥቃቱ ኢላማ የተደረጉት ሴቶች የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በመስከረም ወር 2022 የማሻ አሚኒ ግድያ የቀሰወሰውን ተቃውሞ ሴቶች በስፋት መቀላቀላቸው“የኬሚካል መርዝ በቀል” አስከትሎባቸዋል የሚሉ የመብት ተሟጋቾችም አሉ።
አሜሪካም ምረዛው ለወራት ከተካሄደው ተቃውሞ ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ በመንግስታቱ ድርጅት በኩል ገለልተኛ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቃለች።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ግን ጉዳዩ እንዲጣራ ከማሳሰብ ውጭ ተጠያቂ ያደረጉት አካል የለም።
ጉዳዩን እየተመለከተ ያለው የኢራን የፍትህ ተቋምም እስካሁን ምንም አይነት ግኝቱን ይፋ አላደረገም።