ቱማጅ ሳሊሂ በተላለፈበት የሞት ቅጣት ፍርዱ ላይ ይግባኝ ለማለት 20 ቀናት አለው
ኢራናዊው ራፐር ቱማጅ ሳሊሂ ተቃዋሚዎችን በመደገፉ በሞት እንዲቀጣ እንደተፈረደበት ጠበቆቹ አስታወቁ።
ቱማጅ ሳሊሂ በፈረንጆቹ 2022 ላይ ተገቢ ካልሆነ የሂጃብ አለባበስ ጋር ተያይዞ ፖሊስ ጣቢያ ከገባች በኋላ የተገደለችውን ኢራናዊ ሴት ሞትን ተከትሎ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ደግፎ ዘፍኗል ነው የተባለው።
ኢራናዊው ራፐር ሳሊሂ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረው በፈረንጆቹ ጥቅምት 2022 ሲሆን፤ ለእስር የተዳረገውም ተቃውሞዎችን በመደገፍ በይፋ መግለጫ ከሰጠ በኋላ ነው።
በብዙ ተደራራቢ ወንጀሎች የተከሰሰው ቱማጅ ሳሊሂ በፈረንጆቹ በሰኔ ወር 2023 ላይ በ6 ዓመት ከ3 ወር እስራት ቅጣት ከተፈረደበት በኋ በዋስ መለቀቁ ይታወሰል።
ሆኖም ግን በያዝነው 2024 ታህሳስ ወር ላይ የኢስፋሃን አብዮታዊ ፍርድ ቤት ኢራናዊው ራፐር ቱማጅ ሳሊሂ ተጨማሪ አደዲስ ክሶችም መመስረቱ ነው የተነገረው።
ቱማጅ ሳሊሂ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አሚር ሬይሰን በጉዳዩ ላይ ለሻርቅ ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ፤ አብዮታዊው ፍርድ ቤት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ችላ በማለት፤ ከባድ የቅጣት የሚያስከትሉ ክሶችን መመስረቱን አስታውቀዋል።
ኢራናዊው ራፐር ሳሊሂ በሙስና፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በመገደብ፣ በትጥቅ በታገዘ አመጽ እና መንግስት ላይ ፕሮፓጋንዳ በማሰራጨት ከቀረቡበት ክሶች መካከል መሆናቸውንም ጠበቃው ተናግሯል።
ይህንን ተከትሎ የኢስፋሃን አብዮታዊ ፍርድ ቤት ቱማጅ ሳሊሂን በሞት እንዲቀጣ የፈረደ ሲሆን፤ ሙዚቀኛው በተላለፈበት የሞት ቅጣት ፍርዱ ላይ ይግባኝ ለማለት 20 ቀናት አለው ተብሏል።
ከሙዚቀኛው ጠበቆች አንዱ የሆነው አሚር ሬሲያን ራፐሩ የተላለፈበትን ብይን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል።
ኢራናዊው ራፐር ሳሊሂ የሞት ቅጣት ፍርድ ዙሪያ ከኢራን መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።
የ22 ዓመቷ ኢራናዊት ኩርድ ማህሳ ጸጉርሽን በትክክል አልሸፈንሽም በሚል በቴህራን የደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር ከዋለች ከሶስት ቀናት በኋላ በእስር ላይ እያለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ነው።
የማህሳ አሚኒ ሞት ታዲያ በኢራን ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ማዕበል መቀስቀሱም አይዘነጋም።
የማህሳን ሞት ተከትሎ በኢራን የተቀሰቀሰው ከባድ ተቃውሞ የኢራን መንግስት ቴሌቭዥን እስከመጥለፍ የደረሰ ድርጊት የተስተዋለበትም ጭምር መሆኑ ይታወቃል።