የኢራን እና እስራኤል ጠላትነት እንዴት ጀመረ?
ለአርስት አመታት ስውር ጦርነት ሲያካሄዱ የነበሩት የመካከለኛው ምሰራቅ በላጣዎች ኢራን እና እስራኤል ወደ ይፋዊ ጦርነት ገብተዋል
የኢራን እና እስራኤል ጠላትነት እንዴት ጀመረ?
ለአርስት አመታት ስውር ጦርነት ሲያካሄዱ የነበሩት የመካከለኛው ምሰራቅ በላጣዎች ኢራን እና እስራኤል ወደ ይፋዊ ጦርነት ገብተዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል መሬት ላይ 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖችን በማስወንጨፍ ጥቃት አድርሳ ነበር።
ኢራን ይህን ጥቃት ያደረሰችው እስራኤል ሳታደርሰው አትቀርም በተባለ የአየር ጥቃት በሶሪያ ደማስቆ የሚገኘው ኢምባሲዋ መመታቱን እና ወታደሮቿ መገደላቸውን ነው።
ኢራን ላደረሰችው ጥቃት ምላሽ እንደምትሰጥ ስትዝት የነበረችው እስራኤልም በዛሬው እለት በኢራን መሬት ላይ ጥቃት ማድረሷ ተዘግቧል። በዚህም በሁለቱ የቀጣናው ባላንጣዎች መካከል ለአስርት አመታት ሲካሄድ የነበረው ስውር ጦርነት ገሀድ ሊወጣ ችሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኔያሚን ኔታንያሁ በፈረንጆቹ ባለፈው ሚያዝያ 13 ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል እና የድሮን ናዳ ማዝነቧን ተከትሎ ሀገራቸው እንደምትበቀል ዝተው ነበር።
ግጭቱ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የተባባሰ ቢሆንም ሁለቱ ሀገራት በጠላትነት መተያየት የጀመሩት ከአስርት አመታት በፊት ጀምሮ ነው።
1979-የምዕራባውያን ወዳጅ እና የእስራኤል አጋር ተብለው የሚጠሩት የኢራኑ መሪ ሞሀመድ ሬዛ ሻህ አዲስ አገዛዝ በተከለው እና ጸረ-እስራኤል በሆነው እስላማዊ አብዮት ከስልጣን ተወገዱ።
1982- እስራኤል ሊባኖስን በወረረችበት ጊዜ የኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ በእዚያ ካሉ የሻይት ሙስሊሞች ጋር በመሆን ሄዝቦላን አቋቋመ።
እስራኤል ይህን ታጣቂ ቡድን በድንበሯ ላይ የሚገኝ አደገኛ ቡድን አድርጋ ማየት ጀመረች።
1983- በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላ የእስራኤል እና የምዕራባውያን ኃይሎች ከሊባኖስ እንዲወጡ አጥፎቶ ጠፊዎችን ተጠቀመ። በዚሁ አመት ህዳር ወር ቦምብ የተጠመደበት መኪና ከእስራኤል ጦር ዋና መቀመጫ ጋር እንዲጋጭ በመደረጉ ምክንያት እስራኤል ከአብዛኛው የሊባኖስ ክፍል ለቃ ወጣች።
1992-94 - አርጀንቲና እና እስራኤል፣ በአርጀንቲና ዋና ከተማ ቡነስ አይረስ በሚገኘው የእስራኤል ኢምባሲ ላይ በ1992 እና በአይሁድ ማዕከል ላይ በ1994 ጥቃት በማድረስ ኢራንን እና ሄዝቦላን ከሰሱ። ጥቃቶቹ እያንዳንዳቸው ከደርዘን በላይ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆነዋል።
ኢራን እና ሄዝቦላ በጥቃቶቹ እጃቸው እንደሌለበት አስተባብለዋል።
2002 -ኢራን ዩራኒየም እያበለጸገች ነው የሚል ሚስጥራዊ መረጃ ይፋ ሆነ፤ ኢራን አስተባበለች።እስራኤል በኢራን ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰቀች።
2006- እስራኤል ከሄዝቦላ ጋር ለአንድ ወር የቆየ ጦርነት አካሄደች። ነገርግን በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቀውን ሄዝቦላን መደምሰስ አልቻለችም።
2009- የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ እስራኤልን "አደጋኛ እና የማይድን ካንሰር" ነች የሚል ንግግር አሰሙ።
2010- በአሜሪካ እና እስራኤል ሳይበለጽግ አይቀርም የተባለ ስቱክስኔት የኮምፒዩተር ቫይረስ የኢራንን የኑክሌር ጣቢያ ለማጥቃት ጥቅም ላይ ዋለ። ይህ በኢንዱስትሪያል ማሽነሪዎች ላይ የተፈጸመ በይፋ የሚታወቅ የመጀመሪያ ጥቃት ነበር።
2012- የኢራን ኑክሌር ሳይንቲስት ሙስጠፋ አህማዲ-ሮሻል በመኪናው ላይ በተጠመደ ቦምብ ቴህራን ውስጥ ተገደለ። የከተማው ኃላዎች ለዚህ ጥቃት ተጠያቂ ያደረጉት እስራኤልን ነው።
2018- ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሌሎች መሪዎች ጋር ከኢራን የኑክሌር ስምምነት መውጣታቸውን አወደሱ። በግንቦት ወር እስራኤል በሶሪያ የሚገኙትን የኢራን ወታደራዊ መሰረተልማቶችም መታች። በሶሪያው የእርስበእርስ ጦርነት ኢራን በሽር አል አሳድ ደጋፊ ነች።
በ2020- በኢራን ሪቮሉሽናሪ ጋርድ የውጭ አዛዥ የሆነው ጀነራል ቃሴም ሱሌማኒን በአሜሪካ የአየር ጥቃት መገደል አወደሰች። ኢራን ለዚህ ጥቃት በሰጠችው ምላሽ ኢራቅ ውስጥ በሚኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት አድርሳ 100 ወታደሮችን አቁስላለች።
2021- ኢራን ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራሟ ጀርባ አለ ለተባለው ሞሀሰን ፋኪሪ ዛዴህ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ አደረገች።
2022- የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያኢር ላፒድ ኢራን ኑክሌር እንዳይኖራት ለማድረግ የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራረሙ።
በ2024- እስራኤል በተጠረጠረችበት የኢራን የደማስቆ ኢምባሲ ጥቃት ሁለት ጀነራሎችን ጨምሮ ሰባት የረቮሉሽነሪ ጋርድ ወታደሮች ተገደሉ።
እስራኤል ይህን ጥቃት አድርሳለች የሚለውን ክስ አላመነችም፤ አላስተባበለችም።
ኢራን ባልተጠበቀ ሁኔታ ሚያዝያ 13 በእስራኤል የድሮን እና የሚሳይል ናዳ አዘነበች።
ይህ እስራኤል በዛሬው እለት በኢራን ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት እንድታደርስ አነሳስቷታል።
(በጹሁፍ የተጠቀሱት ጊዜዎች ሁሉም እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር የሆኑ ናቸው።)