አውሮፖ በቅኝ ግዛት ዘመን ለፈጸሙት በደል ይቅርታ ብቻውን በቂ ነው?
አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት ዘመን በሰዎች ላይ ከባድ ጥፋት ማድረሳቸውን ለአሁኑ ትውልድ ማስተማር አለባቸውም ተብሏል
እስካሁን ኔዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን እና ቤልጂየም ይቅርታ ጠይቀዋል
የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን ጨምሮ ላለፉት 150 ዓመታት በርካታ በደሎችን ስለማድረሳቸው የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ።
እነዚህ የበለጸጉ የአውሮፓ ሀገራት በታዳጊ ሀገራት ላይ ላደረሱት በደል በየጊዜው በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ዩሮ ኒውስ አውሮፓ በቅኝ ግዛት ዘመን ለፈጸሙት በደል ይቅርታ ብቻውን ሊበቃ ይችላል? ሲል ባለሙያን አነጋግሮ ሰፊ ዘገባ ሰርቷል።
በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ዙሪያ በሚሰራው ሂውማን ራይትስ ዋች ውስጥ የአውሮፓ ዘረኝነት ጥቃቶች አጥኚ ተመራማሪና የሆኑት አልማዝ ተፈራ በጉዳዩ ዙሪያ ከዩሮ ኒውስ ጋር ቃለመጠይቅ አድርገዋል።
- ቤልጂየም በቅኝ ግዛት ዘመን በዲሞክራቲክ ኮንጎ በሰራችው ጥፋት መጸጸቷን ገለጸች
- ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ዘመን በአፍሪካ ለመፈጸመችው በደል ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጠየቀች
ተመራማሪዋ በቃለ መጠይቃቸው እንዳሉት አውሮፓ በቅኝ ግዛት ዘመን የፈጸመችውን በደል አምና ይቅርታ ለመጠየቅ 150 ዓመታት እንደፈጀባት ተናግረዋል ።
አውሮፓውያን በይፋ ይቅርታ መጠየቃቸው መልካም ጅማሮ ነው የሚሉት ተመራማሪዋ ተጎጂዎችን ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ የሚያደርጉ ስራዎችን መጀመር አለባቸውም ብለዋል።
አውሮፓ በቅኝ ግዛት እና ባሪያ ንግድ መልክ በአፍሪካ እና በሌሎች ሀገራት ላይ ያደረሱት በደል ከይቅርታ በላይ ድርጊት እንደሚፈልግም ጠቁመዋል።
ኔዘርላንድ ፣ዴንማርክ፣ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን ፣ ቤልጂየም እና የአውሮፓ ህብረት በይፋ በቅኝ ግዛት ዘመን ላደረሱት በደል ይቅርታ ጠይቀዋል።
እንዲሁም የቀድሞው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ ጆን ፖል ቤተክርስቲያኗ በቅኝ ግዛት እና ባሪያ ንግድ ዘመን ላደረገችው ተሳትፎ በህይወት በነበሩበት ወቅት ይቅርታ ጠይቀዋል።
ጀርመን በአፍሪካዊቷ ናሚቢያ ላደረሰችው በደል በይፋ ይቅርታ መጠየቋም ይታወሳል።
የቤልጂየም ንጉስ ባሳለፍነው ዓመት ወደ ዲሞክራቲክ ጎንጎ ተጉዘው ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ሀገራቸው ለፈጸመችው በደል ይቅርታ መጠየቋን ገልጸዋል።
እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት ለበደላቸው ይቅርታ መጠየቃቸው ጥሩ ቢሆንም የተለየ ጉዳት የደረሰባቸው ጎሳዎች እና ሌሎች ማህበረሰቦች ካሳ መስጠት እና ሌሎች ድጋፎች ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተመራማሪዋ ጠቁመዋል።
እንዲሁም እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት በቅኝ ግዛት እና የባሪያ ንግድ ወቅት የሰሩትን በደል ለአሁኑ ትውልድ በስርዓተ ትምህርት መልክ ተቀርጾ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ስህተት መስራታቸውን ማወቅ አለባቸው ተብሏል።