ላሚን ያማል ከሮናልዶ እና ሜሲ የተሻለ እግር ኳስ ተጫዋች ሊሆን ይችል ይሆን?
ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስፔናዊው ታዳጊ በዚህ ትውልድ ውስጥ ካሉት ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ሲል አሞካሽቶታል
ተጫዋቹ አሁን በሚገኝበት እድሜ ከሮናልዶ እና ሜሲ ጋር መነጻጸሩ ተጽእኖ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል የስፖርት ተንታኞች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው
ላሚን ያማል ከሮናልዶ እና ሜሲ የተሻለ እግር ኳስ ተጫዋች ሊሆን ይችል ይሆን?
የ17 አመቱ ታዳጊ ስፔናዊ እግር ኳስ ተጫዋች ላሚን ያማል በትውልዱ ውስጥ ከሚገኙ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል እንዱ ነው ሲል ክርስቲያኖ ሮናልዶ አሞካሽቶታል፡፡
በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ በመሰለፍ ባደረገው እንቅስቃሴ አለምአቀፋዊ ትኩረትን ያገኝው ያማል ቀጣዩ ሮናልዶ ወይም ሜሲን የሚተካ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሊሆኑ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
በባርሴሎና የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ላማሲያ ያደገው ስፔናዊ ባሳለፍነው አመት ዋናውን ቡድን ተቀላቀሎ መጫዋት ጀምሯል፡፡
ታዳጊው በወጣትነት እድሜው እያሳየ የሚገኘው የእግር ኳስ ክህሎት በብዙዎች ተስፋ የተጣለበት ሲሆን አቅሙን እና ልምዱን እያዳበረ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በትውልዱ ከሚታዩ ምርጥ ተጫዋቾች ምናልባትም በሮናልዶ እና ሜሲ ደረጃ በስኬቱ ሊጠራ እንደሚችል እየተነገለት ነው፡፡
ፖርቹጋላዊው የአምስት ጊዜ ባላንዶር አሸናፊ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስለተጫዋቹ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ “ላሚን ያማል ትልቅ አቅም ያለው ተጫዋች ነው፤ እኔ እና ሊዮኔል ሜሲ ያላሳካናቸውን ስኬቶች ሊያሳካ እንደሚችል እምነት አለኝ” ብሏል፡፡
ስፔንን የመሰለ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ መታቀፉ በልምድ እና አቅም እንዲዳብር እንደሚረዳው የተናገረው ሮናልዶ በዚህ ትውልድ ውስጥ ከሚጠሩ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው ብሏል
በተጨማሪም ምንም አይነት ጉዳት ወይም ችግር ካላጋጠመው በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ገልጿል፡፡
ላሚን ያማል ባሳለፍነው አመት ዋናውን የባርሴሎና ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ በተሰለፈባቸው 56 ጨዋታዎች 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡
በተመሳሳይ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው 16 ጨዋታወች ደግሞ 3 ግብ ያስቆጠረ ሲሆን 9 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቅብሏል፡፡
ላሚን ያማል በወጣትነት እድሜው እያሳየ በሚገኝው የእግር ኳስ ችሎታ አሁንም መነጋገርያ መሆኑን ቀጥሏል፡፡
አንዳንዶች ተጫዋቹ አሁን በሚገኝበት እድሜ በእግር ኳስ በርካታ ስኬት ከተቀዳጁት ሮናልዶ እና ሜሲ ጋር መነጻጸሩ ተጽእኖ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ላሚን ያማል እያሳየ በሚገኝው አቋም እንዲቀጥል ምሳሌ ሊሆነው የሚችል ከተጽእኖ የሚከላከለው አጋዥ ያስፈልገዋልም ነው የተባለው፡፡