የአሜሪካው ኤፍ 22 የጦር ጄት የአየር ላይ የበላይነት ዘመን እያበቃ ይሆን?
የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት የውጊያ ዝግጁነት ወደ 40.19 በመቶ አሽቆልቁሏል

የአሜሪካ አየር ኃይል እምብዛም ጥቅም አልሰጠኝም ያለውን F-22 ከአገለግሎት ውጪ እንዲሆን እየጠየቀ ነው
አሜሪካ ከምትተማመንባቸው የጦር ጄቶች አንዱ የሆነው እና በአየር ላይ ውጊያ የበላይ የሆነው የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት ተልዕኮዎችን የመፈጸም አቅሙ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ተነግሯል።
የአሜሪካው ዘ ናሽናል ኢንተረስት የተባለው ድረ ገጽ ይዞት በወጣው መረጃ ባለፉት ዓመታት የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት የውጊያ ዝግጁነት ወደ 40.19 በመቶ አሽቆልቁሏል።
የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት የውጊያ ዝግጁነት ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ቅደም ተከተላቸው 57.4 በመቶ እና 52 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን ወደ 40.19 በመቶ መውረዱ ነው የተገለጸው።
ለጦር ጄቱ የውጊያ ዝግጁነት አቅም መውረድ ውስጥ አንዱ የአገልግሎት ጊዜያቸው ወደ ማብቂያው የቀረቡ የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄቶች በአዳዲሶቹ ላይ ሸክም መሆናቸው እንዳልቀረ ተገምቷል።
የአሜሪካ አየር ኃይል እምብዛም ጥቅም አልሰጠኝም ያለውን F-22 የጦር አውሮፕላን ምንም እንኳ የአገለግሎት ዘመኑ የሚያበቃበት ጊዜ ገና ቢሆንም ከፈረንጆቹ 2021 ጀምሮ ከአገለግሎት ውጪ እንዲሆን እየጠየቀ ነው።
አየር ኃይሉ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 32 ኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄቶች ከአገለግሎት ውጪ እንዲሆኑ እቅድ ቢይዝም፤ የአሜሪካ ኮንግረስ እቅዱን ውድቅ በማድረግ እስከ 2028 አገለግሎት ላይ እንዲቀጥሉ አዟል።
ኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት የአገለግሎት ዘመኑን ለማራዘም የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነም ነው የተነገረው።
ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው የኤፍ 22 (F-22) የጦር ጄት ሞተር አምራች ለሆነው ፐራት ኤንድ ዊትኒ ኩባንያ ለ3 ዓመታት የሚቆይ የ1.5 ቢሊየን ዶላር ኮንትራት የተሰጠው ሲሆን፤ ይህምም የጦር ጄቶን ሞተር አቅም ለማጠናከር የሚውል ነው ተብሏል።
የአሜሪካ አየር ኃይል የጦር አውሮፕላች የውጊያ ዝግጁነት በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ በቅርቡ የወጣ ሪፖርቱ ማላከቱ ይታወሳል።
“ሚሊተሪ ዎች” የተባለው ጋዜጣ ይዞት እንደወጣው ሪፖርት ከሆን የአሜሪካ አየር ኃይል የውጊያ ዝግጁነት በ2024 አማካይ 67.15 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ብሏል።
ይህም ከዚያ በፊት ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉ የተመላከተ ሲሆን፤ ለአብነትም በ2023 አማካይ የዝግጁነት መጠን 69.92 በመቶ፤ እንዲሁም በ2022 ደግሞ 71.24 በመቶ አንደነበረም ሪፖርቱ አመላክቷል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ 5ኛ ትውልድ የሚባሉት እንደ "F-22" እና "F-35" ያሉ የውጊያ ጄቶች ለአሜሪካ አየር ኃይል የውጊያ ዝግጁነት ማሽቆልቆል ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።
ምክንያቱ ደግሞ ለጥገና ዋጋ ከፍተኛ ወጪ ስለሚጠይቁ እና የምርት መዘግየት እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል።