አይኤስ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ዛተ
ዛሬ ምሽት አርሰናል በኤምሬትስ ባየርሙኒክን ሪያል ማድሪድ ደግሞ በሳንቲያጎ በርናባው ማንቸስተር ሲቲን ያስተናግዳሉ
ስፔን እና ፈረንሳይ የሽብር ጥቃት ዛቻውን ተከትሎ በስታዲየሞች ዙሪያ የጸጥታ ሃይሎችን በስፋት አሰማርተዋል
አይኤስ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በሚደረጉባቸው ስታዲየሞች ላይ የሽብር ጥቃት እንደሚፈጽም ዛተ።
የሽብር ቡድኑን መልዕክቶች የሚያሰራጨው አል አዛይም ፋውንዴሽን የተሰኘ የሚዲያ ተቋም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች የሚደረጉባቸው ስታዲየሞች የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ዘግቧል።
ዛሬ ምሽት አርሰናል ከባየርሙኒክ የሚጫወቱበት የለንደኑ ኤምሬትስ እና ሪያል ማድሪድ የእንግሊዙን ማንቸስተር ሲቲ የሚያስተናግድበት ሳንቲያጎ በርናባው ከተዘረዘሩት ውስጥ ይገኙበታል።
በነገው እለት ባርሴሎና ወደ ፈረንሳይ ተጉዞ ፒኤስጂን የሚገጥምበት ፓርክ ደ ፕሪንስ እና የአትሌቲኮ ማድሪድ እና ዶርትሙንድ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የሚደረግበት ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየምም አይኤስ “ሁሉንም ግደሏቸው” ከሚል ጽሁፍ ጋር ባጋራው መልዕክት ስማቸው ሰፍሯል ብሏል ዩሮ ኒውስ በዘገባው።
የአርሰናል እና ባየር ሙኒክ የመልስ ጨዋታ የሚያስተናግደው የጀርመኑ አሊያንዝ አሬናም የአይኤስ ኢላማ መሆኑን የሚያሳዩ ምስሎች ባለፈው ሳምንት ወጥተዋል።
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የሽብር ቡድኑ የጥቃት ዛቻ በተመለከተ መረጃ እንደደረሰውና ጨዋታዎቹ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄዱ አስታውቋል።
የፈረንሳይ እና ስፔን የጸጥታ ተቋማትም ጥቃት እንዳይደርስ በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ነው ተብሏል።
ተመልካቾች ተረጋግተው ወደ ስታዲየም እንዲመጡ የጠየቁት የስፔን የስፖርት ሚኒስትር ፒላር አልግሪያ፥ በማድሪድ ከ2 ሺህ በላይ ፖሊሶች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒንም በነገው እለት ፒኤስጂ ከባርሴሎና በሚያደርገው ጨዋታ የጸጥታ ስጋት እንዳይከሰት የጸጥታ አካላት በብዛት ይሰማራሉ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አይኤስ ከዚህ ቀደም በስፖርት ማዘውተሪያዎች ላይ ጥቃት ቢፈጽምም አስቀድሞ የጥቃት ዛቻ ሲያሰማ የዛሬው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።