አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ከ14 አመት በኋላ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቀለ
መድፈኞቹ የፖርቹጋሉን ፖርቶ በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ አውሮፓው መድረክ እየተመለሱ መሆኑን አሳይተዋል
በኤምሬትሱ ፍልሚያ ዴቪድ ራያ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ክለቡን ታድጓል
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ከ14 አመት በፊት ያስመዘገበውን ድል በተመሳሳይ ክለብ እና የውድድር መድረክ ደግሞታል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 9 2010 ፖርቶን 5 ለ 0 (በደርሶ መልስ ውጤት 6 ለ 2) በማሸነፍ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት መድፈኞቹ፥ ትናንት ምሽትም በኤምሬትስ የፖርቹጋሉን ክለብ በመርታት ሩብ ፍጻሜ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
ከሜዳቸው ውጭ 1 ለ 0 ተሸንፈው የተመለሰው የሚኬል አርቴታ ቡድን በኤምሬትስ በሊዮናርዶ ትሮሳርድ ጎል አሸንፎ ድምር ውጤቱ አቻ ሆኗል።
ከፍተኛ ትንቅንቅ የታየበት ጨዋታ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርቶም መድፈኞቹ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል።
ከ14 አመት በፊት አርሰናል ፖርቶን በኤምሬትስ 5 ለ 0 በረታበት ጨዋታ ኒክላስ ቤንድትነር ሶስት ጎሎችን በማስቆጠር ሲነሳበት የነበረውን ወቀሳ ማስረሳቱ ይታወሳል።
በትናንቱ ጨዋታ ደግሞ እንደ ቤንድትነር ጎል አስቆጣሪ ተጫዋች ሳይሆን ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ ነው የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበው።
ራያ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ክለቡን ለጓጓለት ድል አብቅቷል፤ ጨዋታው ከእንግሊዛዊው አሮን ራምስዴል የተሻለ ተመራጭነቱን ያሳየበትን እድልም ፈጥሮለታል።
“በጨዋታው መጨረሻ ላይ ምትሃታዊ መንገድ ተጠቅመን ለማሸነፍ ጥረት አድርገናል፤ በስታዲየም ውስጥ የፈጠርነው ስሜትም ከ14 አመት በኋላ ተናፋዊውን ድል እንድናገኝ አድርጎናል” ብለዋል አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታል።
የ2009/2010 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የአርሰናል የአውሮፓ መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያከተመበት እንደሆነ ይነገራል።
ፖርቶን ጥሎ ወደ ሩብ ፍጻሜ የገባው አርሰናል በባርሴሎና 6 ለ 3 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል።
በመልሶ ጨዋታ መደፈኞቹ 4 ለ 1 ሲሸነፉም ሁሉንም ጎሎች ሊዮኔል ሜሲ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።
አርሰናል ከ2010 በኋላ ለሰባት ተከታታይ አመታት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት ያደረጋቸው ጥረቶች ሳይሳኩ መቅረታቸውና በ2017 በባየርሙኒክ በደርሶ መልስ 10 ለ 2 የተሸነፉበት ውጤትም በአሳፋሪነቱ ይወሳል።