በሞስኮ ጥቃት የፈጸመው “አይኤስአይኤስ-ኬ” ማን ነው?
አሜሪካ የአይኤስ የአፍጋኒስታን ክንፍ የሆነው የሽብር ቡድን ከ130 በላይ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብላለች
ቡድኑ ጥቃቱን ስለማድረሱ ያልገለጸችው ሩሲያ በበኩሏ ጣቷን ወደ ኬቭ ቀስራለች
ሩሲያውያን ከትናንት በስቲያ በሞስኮ በተካሄደ የሙዚቃ ድግስ የተገደሉ ወገኖቻቸውን በሀዘን እያሰቡ ነው።
133 ሰዎች ለተገደሉበትና 152 ሰዎች ለቆሰሉበት ጥቃት “አይኤስአይኤስ-ኬ” ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጿል።
የአሜሪካ የስለላ መረጃዎችም ቡድኑ ጥቃቱን ስለመፈጸሙ ማረጋገጣቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግን በሽብር ጥቃቱ ላይ የተሳተፉ 4 ሰዎች ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከመግለጽ ውጪ አይኤስ እጁ እንዳለበት የሚያመላክት መረጃ አልሰጡም።
አሜሪካ ከጥቃቱ በፊት ለሞስኮ የጥንቃቄ መረጃ ማጋራቷን በተመለከተ የወጡ መግለጫዎችንም በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ ከእውነት የራቁ ናቸው በሚል ውድቅ አድርገዋል።
የአይኤስ የአፍጋኒስታን ክንፍ ማን ነው? በሩሲያ ጥቃት የከፈተበት ምክንያትስ?
ኢስላሚክ ስቴት ኮርሳን (አይኤስአይኤስ - ኬ) በ2014 በምስራቃዊ አፍጋኒስታን ነው የተመሰረተው።
ኮርሳን የሚለው ከኋላ ያስከተለው ተቀጽላም ኢራን፣ ቱርክሚኒስታን እና አፍጋኒስታንን ያካተተ የቀድሞ ግዛት መጠሪያን ለመውሰድ ነው።
በአረመኔያዊ እርምጃው በአጭር ጊዜ ስሙ የገነነው የሽብር ቡድኑ በ2018 በርካታ ምልምል ታጣቂዎችን አባል ማድረግ ቢችልም በአሜሪካ እና ታሊባን እርምጃ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ ከአፍጋኒስታን ለቃ ከወጣች በኋላ የቡድኑ ጥቃት መጨመሩን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ አዛዥ ጀነራል ሚኬል ኩሪላ በመጋቢት ወር መግቢያ ለኮንግረንሱ ባቀረቡት ሪፖርት አይኤስ ኮርሳን በአውሮፓ እና እስያ ጥቃቶችን ለመፈጸም የሚያስችለውን አቅም በፍጥነት እያሳደገ ነው ማለታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ጀነራሉ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት ላይ ጥቃት ማድረስ እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።
አሜሪካ በ2021 ከአፍጋኒስታን ከወጣች በኋላ እንደ አይኤስ ኮርሳን ባሉ የሽብር ቡድኖች ላይ ስለላ ለማካሄድ የምታደርገው ጥረት መቀነሱም ስጋት መፍጠሩን ነበር ያነሱት።
የአፍጋኒስታኑ የአይኤስ ክንፍ እስካሁን የፈጸማቸው ጥቃቶች
የታሊባን መንግስትን የሚቃወመው አይኤስ ኮርሳን በአፍጋኒስታንና የተለያዩ ሀገራት በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሟል። ጥቃቱ በመስጂዶች ላይም ጭምር ያነጣጠረ ነው።
ቡድኑ በዚህ አመት በኢራን ከ100 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፉ የሽብር ጥቃቶችን መፈጸሙ ይታወሳል።
በመስከረም ወር 2022ም በካቡል በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ላይ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ፈጽሟል።
ከሶስት አመት በፊት በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ለተፈጸመውና 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ በርካታ አፍጋኒስታናውያን ንጹሃን ለተገደሉበት ጥቃትም ሃላፊነቱን መውሰዱ አይዘነጋም።
በአፍጋኒስታኗ ካንድሃር ከተማ ባለፈው ሳምንት ከባንክ ደመወዛቸውን ለመውሰድ በተሰለፉ የመንግስት ሰራተኞች ላይ በተቃጣው የሽብር ጥቃትም ይሄው ቡድን እጁ እንዳለበት አምኗል።
አይኤስ ኮርሳን ለምን ሩሲያን ያጠቃል?
ተንታኞች የአፍጋኒስታኑ የሽብር ቡድን የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደሚቃወም ያነሳሉ።
“የቡድኑ መሪዎች ባለፉት ሁለት አመታት ፑቲንን በተደጋጋሚ ሲያወግዙ የሚሰሙት ፕሬዝዳንቱ ሙስሊሞችን ይጨቁናል ከሚል እሳቤ ነው” ይላሉ በኒውዮርክ የሚገኘው የጥናት ተቋም ሱፋን ሴንተር ባልደረባው ኮሊን ክላርክ።
ቡድኑ በሞስኮ እና ፑቲን ላይ ቅራኔ ያላቸው የተለያዩ የእስያ ሀገራት ዜጎችን በአባልነት መያዙም ሌላኛው ምክንያት ነው ተብሏል።
አሜሪካ ስጋቷን በገለጸች ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሞስኮ ከሁለት አስርት አመት በኋላ ግዙፉን የሽብር ጥቃት የፈጸመው “አይኤስአይኤስ-ኬ” የጥቃቱን አላማ ከማብራራት ተቆጥቧል።