ከቁርዓን መቃጣል የተቆጡ የአረብ ሀገራት የስዊድን አምባሳደርን ለማብራሪያ ከመጥራት ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት ደርሰዋል
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በትናንትናው እለት ሲከበር በስዊድን መዲና ስቶኮልም ተቃዋሚዎች የቅዱስ ቁርአን ማቃጠላቸው በርካታ ሀገራትን አስቆጥቷል።
በስዊድን ጸረ እስልምና ይዘት ያላቸው ተቃውሞዎች ሲደረጉ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በአረፋ እለት ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በተሰባሰቡበት መስጂድ ዙሪያ ቁርአን በማቃጠል የተገለጸው ተዋውሞ በርካቶችን አስቆጥቷል።
በርካታ የዓለም ሀገራት ተግባሩን መቃወማቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ከቁርዓን መቃጣል የተቆጡ የአረብ ሀገራት የስዊድን አምባሳደርን ለማብራሪያ ከመጥራት ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት መድረሳቸው ተነግሯል።
አረብ ኢሚሬትስ
የስዊድን መንግስት ሀሳብን በነጻት በመግለጽ መብት በሚል ከለላ ቁርዓን ኢንዲቃጠል መደረጉን ተከትሎ የአረብ ኢሚሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስዊድን አምባሳደርን በመጥራት ድርጊቱን እንደሚያወግዝ እና እንደሚቃወም አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ስዊድን ጽንፈኞች ቁርዓን እንዲያቃጥሉ መፍቀዷን አረብ ኢሚሬትስ እንደምትቃወም አስታውቃለች ብሏል።
ሳዑዲ አረቢያ
በስዊድን ከተከሰተው ድርጊት ጋር በተያያዘ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን የሃጅ ተጓዦች የየተቃውሞ መልእክት የተቀበለው የሳዑዲ አረቢያ መንግስትም የቁርዓም መቃጠልን አውግዟል።
የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እነዚህ በጥላቻ የተሞሉ ተደጋጋሚ ድርጊቶች በምንም ምክንያት መቀበል አይቻልም” ያለ ሲሆን፤ “ጥላቻን፣ ማግለልን እና ዘረኝነትን ያነሳሳሉ" ብሏል።
ቱርክ
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን፥ ስዊድን በንግግር ነጻነት ስም ይህን መሰል ነውረኛ ተግባር እንዲደረግ መፍቀድ አልነበረባትም ብለዋል።
“እያንዳንዱ ህጋዊ ነገር ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም” ሲሉም አክለዋል።
ኢራቅ
ኢራቅ በበኩሏ የስዊድን ባለስልጣናት አክራሪ ጽንፈኞች የቁርኣንን ቅጂ እንዲያቃጥሉ ፍቃድ የመስጠት ውሳኔን አውግዘዋል።
የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ይህ አሰቃቂ ድርጊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን ስሜት የጎዳና ያሳዘነ ነው ያለ ሲሆን፤ ልዩነትን በመቀበል፣ የሌሎችን እምነት በማክበር እንዲሁም ሃይማኖቶችን እና መብቶችን በመጠበቅ ለረጅም ጊዜ ሲፎክሩ የነበሩትን ምዕራባውያን ያሳጣ ተግባር ነው ብሏል።
ኢራን
በስዊድን የተፈጸመው የቁርዓን መቃጠል ተግባር ያስቆጣት ኢራንም፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው መግለጫ እንዲህ አይነቱን ጸብ አጫሪ ተግባር አንታገስም ብላለች። የሰዊድን መንግስትም ኃይማቶችን የመጠበቅ እና ቅዱሳን ከመሰደብ የመጠበቅ ኃፊነቱን በአግባ ሊወጣ ይገባል ሲል አሳብቧል።
ግብጽ
በሕዝብ ብዛት ትልቋ አረብ ሀገር የሆነችው ግብፅ በስዲድን የተፈጸመው ተግባር አሳፋሪ ነው ያለች ሲሆን፤ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በአለም ዙሪያ እያከበሩ ያሉ የሙስሊሞችን ስሜት የሚጎዳ ተግባር ብላ ወስዳለች።
ግብጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ በስዊድን የተፈተመውን የቅዱስ ቁርዓን የማቃጠል ተግባርን ያወገዘች ሲሆን፤ በተወሰኑ የአውሮፓ ሀገራት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታየው ቁርዓንን የማቃጠል ተግባር እንደሚያሳስባትም አስታውቃለች።
የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በትናንትናው እለት ሲከበር በስዊድን መዲና ስቶኮልም ከ200 በላይ የሚሆኑት ተቃዋሚዎች በመስጂዱ ዙሪያ ሆነውም በድምጽ ማጉያ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፥ የበዓሉን አከባበርም ለማወክ ሞክረዋል።
አንድ ግለሰብም የቅዱስ ቁርአን ገጾችን በመቦጫጨቅ በእሳት ሲያያዝ ሌሎቹ “አቃጥለው” እያሉ የድጋፍ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ነበር።
የስዊድን ፖሊስ ከዚህ በፊት ሊደረጉ ቁርአንን በማቃጠል ሊደረጉ የነበሩ የተቃውሞ ሰልፎችን ቢያግድም የሀገሪቱ ፍርድቤት የንግግር ነጻነትን ይቃረናል ብሎ ፈቃድ ሰጥቷል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስቴርሰን በሰጡት መግለጫም፥ ቁርአን የማቃጠሉን ጉዳይ “ተገቢ አይደለም ግን ህጋዊ ነው” በሚል አልፈውታል።