ፑቲን ቁርአን በማቃጠል የሚደረግ ተቃውሞን አወገዙ
ፕሬዝዳንቱ “አንዳንድ ሀገራት የሌሎችን ሃይማኖት ማንቋሸሽ እና ጥላቻን ለማንጸባረቅ መሞከር እንደወንጀል አይቆጥሩትም” ሲሉ ተችተዋል
በስዊድን ትናንት የአረፋ በዓል ሲከበር ተቃዋሚዎች ቁርአን ማቃጠላቸው ከባድ ተቃውሞ አስነስቷል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በትናንትናው እለት በስዊድን መዲና ስቶኮልም ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ቁርአን ማቃጠላቸውን አውግዘዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሙሊሞች በሚበዙበት የዳጌስታን ክልል ባደረጉት ጉብኝት “ቁርአን ለሙስሊሞች ቅዱስ መጽሃፍ ነው” ብለዋል።
ይህን ቅዱስ መጽሃፍ ማቃጠልም የጥላቻ መገለጫ እና የእምነቱን ተከታዮች ሆን ብሎ ለጸብ ለማነሳሳት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
“አንዳንድ ሀገራት የሰዎችን የእምነት ነጻናትና ስሜት አያከብሩም፤ የአንድን ግለሰብ እምነት መንካት ወይም ማጥቃትም እንደ ወንጀል አይቆጥሩትም” ሲሉ ወቅሰዋል።
ሩሲያ ግን በወንጀል ህጓ ጭምር የሌሎችን ሃይማኖት ለማንቋሸሽ እና ጥላቻን ለማንጸባረቅ መሞከር በወንጀል እንደሚያስቀጣ መደንገጓን ነው ፕሬዝዳንት ፑቲን ያነሱት።
“ሃይማኖታዊ ጥላቻን ለማስፋፋት የሚደረግ ማንኛውም ድርጊት ወንጀል ነው፤ እኛ ሁሌም በህጎቻችን ላስቀመጥናቸው ነጥቦች ተገዥዎች ነን” ማለታቸውንም አርቲ አስነብቧል።
ትናንት የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በስዊድን ስቶኮልም ሲከበር ከ200 በላይ ተቃዋሚዎች መስጂድ ከበው የጥላቻ ንግግር ሲያሰሙና ቅዱስ ቁርአን ሲያቃጥሉ ታይቷል።
የስዊድን መንግስት ግን “ህጋዊ ግን ተገቢ ያልሆነ” ሲል የገለጸውን የተቃውሞ ሰልፍ የመናገር ነጻነትን ለማክበር በሚል እንዳላስቆመው ነው ያስታወቀው።
ቱርክ በበኩሏ ስቶኮልም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች የአረፋ በዓልን በሚያከብሩበት ወቅት በመስጂድ ዙሪያ የተደረገውን ተቃውሞና የቁርአን ማቃጠል በጥብቅ አውግዛለች።
ስዊድን በንግግር ነጻነት ስም መሰል ነውረኛ ተግባር እንዲደረግ መፍቀድ አልነበረባትም ብለዋል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
በስቶኮልም በሚገኘው የቱርክ ኤምባሲ አቅራቢያ በጥር ወር 2023 በተመሳሳይ በተቃዋሚዎች ቁርአን መቃጠሉን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል።
ሙስሊም እና ኩርድ ጠል ስዊድናውያን አደባባይ በመውጣት የሚያንጸባርቁት መልዕክት በአንካራ ብቻ ሳይሆን ቱርክ፣ አሚሪካ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ግብጽን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት እየተወገዘ ይገኛል።
ሞስኮም ይህን እየተደጋገመ የመጣና የሃይማኖት እኩልነትን የማያከብር ድርጊት በይፋ የተቃወሙትን ሀገራት ተቀላቅላለች።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ሲጀመር የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅትን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረበችው ስዊድን ከቱርክ እስካሁን ድጋፍ አላገኘችም።
የትናንቱ ክስተትም የስቶኮልምን ኔቶን የመቀላቀል ሂደት እንደሚያጓትትባት ነው የሚጠበቀው።