አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊባኖስ ዳግማዊ ጋዛ እንዳትሆን ስጋቱን በመግለጽ ላይ ነው
የመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ወደማይቀር ቀውስ እያመራ ነው ሲል ተመድ ገለጸ።
በእስራኤል እና ሂዝቦላ መካከል ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን ውጥረት ለማርገብ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረበ ይገኛል፡፡
ሆኖም ሁለቱ አከላት እርስበእርስ የሚያደርጉትን ድንበር ተሸጋሪ ጥቃት መጠን ለመጨመር በመዛት ላይ ናቸው፡፡
እስራኤል ቅዳሜ አዳሩን እስከ እሁድ ንጋት ድረስ ከ150 በላይ ሮኬቶች እና ሚሳይሎች ከሂዝቦላ እንደተተኮሰባት አስታውቃለች፡፡
አንዳንዶቹ ሚሳኤሎች እስከዛሬ ደርሰውባቸው በማያውቁ አካባቢዎች መድረሳቸውን ተከትሎ በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቦምብ መጠለያ ውስጥ እንዲከለሉ ተደርጓል፡፡
እስራኤል በሰጠችው የአጸፋ ምላሽ በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ የሂዝቦላ ሮኬት መተኮሻዎችን ማውደሟን አስታውቃለች፡፡
በትላንትናው እለት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እስራኤል ደህንነቷን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረው በሂዝቦላ ላይ የሚደረገው ጥቃት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሂዝቦላ ምክትል መሪ ናይም ቃሲም በበኩላቸው ዛቻ እና ማስፈራሪያዎች የሚያስቆመን ሰዎች አይደለንም የትኛውንም ወታደራዊ ጥቃት ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን ሲሉ ለኔታንያሁ ዛቻ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ቡድኑ ለእስራኤል ጥቃት የሚንበረከክ አይደለም፤ በተቃጣብን ጥቃት ልክ አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጠን እንቀጥላለን ያሉት ምክትል መሪው እስራኤል አለም በይፋ እየተመለከተ ወደ ጦርነት እየጋበዘችን ነው ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በግንኙነት መሳሪያዎች ላይ በደረሰው ፍንዳታ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የቀጠናው ውጥረት ተባብሶ ቀጥሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰሞኑን ወጥረት ተከትሎ ሁለቱም አካላት ወደ ግጭት ከሚያስገቡ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እያወጣ ይገኛል ።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየታየ የሚገኘው ውዝግብ ዳግማዊ ጋዛን እንዳይፈጥር ያሰጋኛል ብሏል።
ዋና ጸሀፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ መካከለኛው ምስራቅ ወደማይቀር ጥፋት እየተንደረደረ ነው ያሉ ሲሆን አሁን ሁለቱ አካላት ወደ ጦርነት መግባታቸው በመካከላቸው ያለውን ልዩነት የሚቀርፍ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡