“ትክክለኛውን እውነት የምናውቀው እኛ ነን፤ ወደ ኢትሃድ ለማሸነፍ ነው የምንጓዘው” - ቡካዮ ሳካ
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ ጨዋታ ማንቸስተር ሲቲ በሜዳው አርሰናልን ያስተናግዳል
መድፈኞቹ በሊጉ በኢትሃድ ካደረጓቸው ጨዋታዎች ያሸነፉት በሶስቱ ብቻ ነው
በእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ዛሬ ማንቸስተር ሲቲ ከአርሰናል ይጫወታሉ።
ማንቸስተር ሲቲ አራቱን የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ጨዋታዎች አሸንፎ አርሰናል ደግሞ በአንዱ ተሸንፎ ነው በኢትሃድ ምሽት 12 ስአት ከ30 ላይ የሚገናኙት።
አርሰናል ባለፈው የውድድር አመት በኢትሃድ ከሲቲ ጋር ያደረገውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ያለምንም ግብ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
በወቅቱም የመድፈኞቹ የመከላከል አካሄድ ሰፊ ትችት ሲነሳበት ነበር።
ቡካዮ ሳካ ግን የሚነሱ ትችቶችን ሁሉ ወደ ጎን ትተን ከኢትሃድ ሶስት ነጥብ ይዘን ለመመለስ ነው ስንሰራ የቆየነው የሚል አስተያየት ሰጥቷል።
ሳካ ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ “እውነት ለመናገር (ለትችቶቹ) አልጨነቅም፤ ምን ለማድረግ ወደ ኢትሃድ እንደምንጓዝ በደንብ እናውቀዋለን፤ ትክክለኛውን እውነት እኛ ነን የምናውቀው፤ (ኢትሃድ) የምንሄደው ለማሸነፍ ነው” ብሏል።
ሁለቱም ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከገጠሟቸው ክለቦች ነጥብ ከተጋሩ በኋላ ነው ተጠባቂውን ፍልሚያ የሚያደርጉት።
ማንቸስተር ሲቲ ከኢንተርሚላን፤ አርሰናል ደግሞ ከአትላንታ በሻምፒዮንስ ሊጉ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
መድፈኞቹ በዛሬው የኢትሃድ ጨዋታ የቁርጭምጭሚት ጉዳት የገጠመውን አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ ወደ ሜዳ ይዘው አይገቡም።
ሳካም የኦዲጋርድ አለመኖር ከፍተኛ ጉዳት መሆኗን ቢያምንም “ከጉዳቱ እስኪመለስ ድረስ ክፍተቱን የሚደፍን መፍትሄ አናጣም” ሲል መናገሩን ስካይን ኒውስ አስነብቧል።
ማንቸስተር ሲቲ ያለፉትን አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በማሸነፍ በ12 ነጥብ በሊቨርፑል በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርሰናል በበኩሉ በሶስቱ አሸንፎ ከብራይተን ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ በ10 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
የምሽቱ ጨዋታ አርሰናልን ቀዳሚ የሚያደርግ አልያም ማንቸስተር ሲቲ ከባለፈው አመት ተቀናቃኙ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት የሚያሰፋ ይሆናል።
አሃዛዊ መረጃዎች ግን የማሸነፍ እድሉ ወደ ማንቸስተር ሲቲ እንደሚያዘነብል ያመላክታሉ።
አርሰናል በኢትሃድ ካደረጋቸው ያለፉት 29 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በሶስቱ ብቻ ነው።