የዩክሬን አየር ኃይል 71 የሩሲያ ድሮኖችን አወደምኩ አለ
አየር ኃይሉ በቴሌግራም ገጹ እንደገለጸው ሌሎች ስድስት ድሮኖች በዩክሬን ኤሌክትሮኒክ ዋርፌር ጥቃት ደርሶባቸው የደረሱበት እንዲጠፉ ተደርጓል
የዩክሬን አየር ኃይል ቡድን ከተተኮሱት 80 የሩሲያ ድሮኖች ውስጥ 71ዱን እሁድ ሌሊቱን ማውደሙን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል
የዩክሬን አየር ኃይል ቡድን ከተተኮሱት 80 የሩሲያ ድሮኖች ውስጥ 71ዱን እሁድ ሌሊቱን ማውደሙን የዩክሬን አየር ኃይል አስታውቋል።
አየር ኃይሉ በቴሌግራም ገጹ እንደገለጸው ሌሎች ስድስት ድሮኖች በዩክሬን ኤሌክትሮኒክ ዋርፌር ጥቃት ደርሶባቸው የደረሱበት እንዲጠፉ ተደርጓል።
ሩሲያ በወረራ ከያዘችው የሉሀንስክ ግዛት ሁለት ጋይድድ ሚሳይሎችንም ማስወንጨፏንም አየር ኃይሉ ገልጿል። አየር ኃይሉ ሚሳይሎች ያደረሱት ጉዳት ስለመኖሩ ወይሜ ስላለመኖሩ ያለው ነገር የለም።
31 ወራትን ያስቆጠረው የዩክሬን -ሩሲያ ጦርነት አሁንም ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።
ዩክሬን በምስራቅ ዩክሬን የተሰማራውን የሩሲየ ኃይል ለማዛባት ባለፈው ነሐሴ ወር በምዕራብ ሩሲያ ክርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት ከፍታ በርካታ ቦታዎች መቆጣጠር ችላ ነበር።
ነገርግን የሩሲያ ኃይሎች ማጥቃታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ወሳኝ የተባለችውን የምስራቅ ዩክሬኗን ፖክሮቭስክ ከተማ ለመያዝ ተቃርበዋል።
ዩክሬን ምዕራባውያን ሀገራት የለገሷትን የረጅም ርቀት ሚሳይሎች ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን እንድትመታ እንዲፈቅዱላት ብትጠይቅም እስካሁን አልፈቀዱላትም።
ፑቲን ምዕራባውያን ለዩክሬን ፍቃድ የሚሰጧት ከሆነ ቀጥተኛ ጦርነት ይቀሰቀሳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዩክሬን ሩሲያን ድል የማድረግ ጉዳይ በምዕራባውያን አጋሮቿ በተለይም በአሜሪካ ድጋፍ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ፕሬዝደንት ዘለንስኪ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎችን ከግዛቷ ለማስወጣት እየተዋጋች ሲሆን ሩሲያ ደግሞ አራት የምስራቅ ዩክሬን ግዛቶችን ሙሉ በሙሉ ለመጠቅለል ማጥቃቷን ቀጥላበታለች።