እስራኤል በኢራን ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት ምን አይነት መሳሪያ ትጠቀማለች?
እስራኤል ልትጠቀማቸው የምትችላቸውን መሳሪያዎች የሚያሳይ መረጃ አፈትልኮ ወጥቷል
በኢራን ጥቃት የተሰነዘረባት እስራኤል የምትወስደው የአጸፋ እርምጃ እየተጠበቀ ነው
እስራኤል በኢራን ላይ ልትወስደው በምትችለው የአጸፋ እርምጃ ልትጠቀማቸው የምትችለውን መሳሪያ የሚያሳይ መረጃ አፈትልኮ ወጥቷል።
የእንግሊዙ ታይምስ መጽሄት ከአሜሪካ መከላከያ የደህንነት ተቋም ሾልኮ ወጣ በተባለ ሰነድ ላይ የተቀመጡ የመሳሪያ አይነቶችን ይፋ አድርጓል።
ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እንደወጣ በሚያሳየው እና በቴሌግራም ላይ ተለቀቀው መረጃ እስራኤል እያደረገች ያለውን ዝግጅትና እንቅቀሴዎች የሳተላይት ምስሎች እና የደህንነት ምንጮችን ዋቢ ያደረገ ነው ተብሏል።
በዚህም ለየት ያለ ሚሳኤሎችን የታጠቁ የእስራኤል የጦር ጅቶች ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሲያደርጉ ተመላክቷል።
የእስራኤል የደህንነት ምንጭ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፣ መረጃው ከአሜሪካ እጅ አፈትልኮ መውጣቱ እስራኤል ጥቃት ለመፈጸም ያቀደችበትን ጊዜ እና ስትራቴጂ እንድትቀይር አስገድዷታል።
የእስራኤል ኢላማም ምን ነው?
ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሾልኮ ወጣ በተባለው ሰንድ ላይ እስራኤል በኢራን ላይ በምትፈጽመው የአየየፋ እርምጃ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና ባሲጅ የተባለው ወታደራዊ ሃይል ዋነኛ ኢላማ ናቸው ተብሏል።
እስራኤል ምን አይነት መሳሪያ ትጠቀማለች?
ከአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የአጸፋ እርምጃ ከምትጠቀማቸው የመሳሪያ አይነቶች ውስጥ የተወሰኑትን ይፋ አድርጓል።
ከእነዚህም ውስጥ ከተዋጊ ጄቶች ላይ የሚተኮሱ ከአየር ላይ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ይገኙበታል የተባለ ሲሆን፣ ይህም የሌላ ሀገር የአየር ክልል መጠቀም ሳይያስፈልግ ጥቃት መሰንዘር የሚያስችል ነው።
ከሚሳኤሎቹ ውስጥም "ጎልደን ሆራይዘን" እና ሮክስ 2 የተባሉ ከአየር ላይ የሚተኮሱ ሚሳኤሎችን ያካተተ ነው።
"ሮክስ" የሚል መጠሪያ ያለው የባላስቲክ ሚሳዔል ከአየር ወደ ምድር የሚተኮስ ሲሆን፣ ከኤፍ 16 እና ኤፍ 35 የጦር ጄቶች ላይ መተኮስ የሚችል ነው።
"ጎልደን ሆራይዘን" የተባለው ሚሳኤል ከአየር ላይ የሚተኮስ ሲሆን: እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ያለን ኢላማ መምታት የሚችል ነው ተብሏል።