ኢራን የእስራኤልን የአየር መከላከያ የሚጥስ ጥቃት መፈጸም እችላለሁ አለች
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በካይሮ ከፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጥቃት የሚፈጸምባቸው የኢራን ኢላማዎች እቅድ ማጽደቃቸው ተዘግቧል
የኢራን አብዮታዊ ዘብ እስራኤል በቴህራን ላይ ጥቃት ከማድረስ እንድትቆጠብ አሳስቧል።
የአብዮታዊ ዘቡ አዛዥ ሁሴን ሳላሚ በዛሬው እለት በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት “በየትኛውም ጊዜና ቦታ ወረራና ጥቃት ካደረሳችሁብን (በእስራኤል) ተመሳሳይ ስፍራ ላይ ከባድ የአጻፋ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።
የቴህራን ሚሳኤሎች የእስራኤል የአየር መከላከያ ጥሰው ጥቃት ማድረስ እንደሚችሉም ነው የተናገሩት።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዡ እስራኤል በጥቅምት ወር መጀመሪያ ለተፈጸመባት የባለስቲክ ሚሳኤል አጻፋዊ እርምጃ ለመውሰድ በተዘጋጀችበት ወቅት ነው ማሳሰቢያውን ያሰሙት።
ኤቢሲ ኒውስ የእስራኤል ምንጮቹን ጠቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በእስራኤል ሊመቱ የታሰቡ የኢራን ኢላማዎችን በተመለከተ የቀረበውን እቅድ ማጽደቃቸውን ዘግቧል።
በሌላ በኩል እስራኤል ልትፈጽመው ላቀደችው የአጻፋ ጥቃት የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱና ውጥረቱን ለማርገብ በሚል በኳታር፣ ሳኡዲ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ እና ዮርዳኖስ ጉብኝት ያደረጉት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ግብጽ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የመከሩ ሲሆን፥ ካይሮ የእስራኤልና ኢራን ግጭት ቀጠናዊ መልክ እንዳይዝ ጥንቃቄ ያሻል ማለቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
በኢራን ላይ የአጻፋ እርምጃው አይቀሬ ነው ያለችው እስራኤል ግን በሊባኖስ ከሄዝቦላህ እና በጋዛ ከሃማስ የምታደርገውን ጦርነት አጠናክራ ቀጥላለች።
የእስራኤል ጄቶች ዛሬ በሶሪያ የወደብ ከተማዋ ላታኪያ ድብደባ ፈጽመዋል፤ አሜሪካ ደግሞ በየመን አምስት የሁቲ ታጣቂዎች የመሳሪያ ማከማቻዎችን መምታቷን አስታውቃለች።
የእስራኤልና አጋሯ አሜሪካ በኢራን በሚደገፉ ሃይሎች ላይ የከፈቱት የተጠናከረ እርምጃ ወቅታዊውን የመካከለኛው ውጥረት እያባባሰው እንዳይሄድ ከፍ ያለ ስጋት ደቅኗል።
በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የአደራዳሪነት ሚና የነበራት ኳታር ባለፉት ሶስት እና አራት ሳምንታት የጋዛ ተፋላሚ ወገኖችን ማግኘት አልቻልኩም ብላለች።
በደቡባዊ ሊባኖስ ከሄዝቦላህ ጋር የሚካሄደው ውጊያና የአየር ድብደባም ቤሩትን ሌላኛዋ ጋዛ ሳያደርግ በአጭር ጊዜ የሚቋጭ አይመስልም።