ኢራን ስልጣን ከጨበጡት የሶሪያ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ማድረጓን ማመኗ ተነገረ
ሞስኮም በተመሳሳይ ከአዲሶቹ መሪዎች ጋር መነጋገሯን እና በሶሪያ ያለው የጦር ሰፈሯ ጉዳት እንደማይደርስበት ዋስትና እንደሰጧት አስታውቃለች

ሀገሪቱን ለ 24 አመታት ያስተዳደረው አላሳድም ወደ ሩሲያ በመኮብለል ተጠልሏል
ኢራን ስልጣን ከጨበጡት የሶሪያ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ማድረጓን ማመኗ ተነገረ።
ኢራን አጋሯ የነበሩት የሶሪያው የረጅም ጊዜ መሪ በሽር አላሳድ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በአዲሱ የሶሪያ አመራር ውስጥ ካሉ አማጺ ቡድኖች ጋር መነጋገሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ኢራን ይህን ያደገችው በሁለቱ ሀገራት መካከል ሊኖር የሚችለውን የጠላትነት ግንኙነት ለመከላከል ስትል ነው።
የቀድሞ የአልቃ ኢዳ አጋር በነበረው በሀያት ታህሪር አል ሻም የሚመሩት ታጣቂ ቡድኖች ያደረሱት መብረቃዊ ጥቃት በመካከለኛው ምስራቅ በትውልዶች ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ጉልህ ክስተት ሆኗል።
የአሳድ መውደቅ ኢራን እና ሩሲያ በቀጣናው ሊኖራቸው የሚችለውን ተጽዕኖም የሚቀንስ ነው ተብሏል።
በደማስቆ የነበረውን ወሳኝ አጋራቸውን ያጡት የኢራን ኃይማኖታዊ መሪዎች ከአዲሱ አመራር ጋር ለመነጋገር መገደዳቸውን ሮይተርስ ያነጋገራቸው አንድ የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።
"ንግግሩ ግንኙነታቸውን ለማረጋጋት እና በቀጣናው ተጨማሪ ውጥረትን ለማስወገድ ወሳኝ ነው"ብለዋል ባለስልጣኑ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ በትናንትናው እለት ከ2015 ጀምሮ የበሽር አላሳድ አገዛዝን ለመርዳት በሶሪያ የተሰማሩ ወታደሮችን እንደሚያስወጡ አመላክተዋል።
አራግቺ አክለውም ባለፈው ሳምንት በሽር አላሳድ የሶሪያ ጦር የአማጺያኑንን ግስጋሴ መግታት አለመቻሉ እንዳስደነገጣቸው እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
የታጠቁት ተቃዋሚዎች ለበርካታ የቀጣናው አካላት ትብብር ማድረግ እንደሚፈለልጉ የሚገልጽ መልእክት ልከዋል።
ሞስኮም በተመሳሳይ ከአዲሶቹ መሪዎች ጋር መነጋገሯን እና በሶሪያ ያለው የጦር ሰፈሯ ጉዳት እንደማይደርስበት ዋስትና እንደሰጧት አስታውቃለች።
የሶሪያ አማጺያን ለበርካታ አመታት በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ መሽገው ከቆዩ በኋላ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ባካሄዱት መብረቃዊ የሚባል ጥቃት የበሽር አላሳድ መቀመጫ የሆነችውን ደማስቆን በትናንትናው እለት መቆጣጠር ችለዋል።
ይህን ተከትልም ሀገሪቱን ለ 24 አመታት ያስተዳደረው አላሳድም ወደ ሩሲያ በመኮብለል ተጠልሏል፤ ሩሲያም ለእሱ እና ለቤተሰቦቹ ጥገኝነት እንደሰጠቻቸው ተገልጿል።