ሩሲያ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር-አል አሳድ ስልጣን ለቀው ከሀገር መኮብለላቸውን ተከትሎ ምን አለች?
አሳድ በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ ካሉ ሌሎች አካላት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ሀገር ለቀው መውጣታቸውን ሩሲያ አስታውቃለች
የበሽር አል አሳድ ቁልፍ አጋር ነበረችው ሩሲያ ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ወታደራዊ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች
ሩሲያ የሶሪያው ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ትእዛዝ ካስተላለፉ በኋላ ስልጣናቸውን ለቀው ከሀገር መኮብለላቸወን አስታወቀች።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ በግጭቱ እየተሳተፉ ካሉ ሌሎች አካላት ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ከሀገር መውጣታቸውን ሩሲያ አስታውቃለች።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ፤ ከስልጣን የተነሱት የሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ “ከሌሎች የትጥቅ ትግል ተሳታፊዎች" ጋር በተደረገ ድርድር ስራቸውን እና ሀገራቸውን በመልቀቅ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ መመሪያ በመስጠት መሆኑን አስታውቋል።
በነዚህ ድርድሮች ላይ ሩሲያ እንዳልተሳተፈች ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፤ በሶሪያ የሚገኙ የሩሲያ ወታደራዊ ሰፈሮች በተጠንቀቅ ላይ እንደሆኑ እና አአሁን ላይ የተደቀነባቸው ስጋት እንደሌለም አስታውቋለረ።
ሩሲያ "ከሁሉም የሶሪያ ተቃዋሚ ቡድኖች" ጋር ግንኙነት እንዳላትም ገልጻለች።
ሩሲያ የበሽር አል አሳድ ቁልፍ አጋር ነበረች ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንቱ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ ወታደራዊ ድጋፍ ስትሰጥ እንደቆየች ይታወቃል።
ለ24 ዓመታት የዘለቀው የበሽር አል አሳድ አገዛዝ ማብቃቱን የሶሪያ ጦር አዛዥ ለሀገሪቱ ጦር አመራሮች ማሳወቃቸው ሮይተረስ ምንጮች ጠቅሶ መዘገቡ ይታወቃል።
ሶሪያን ለ24 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ዛሬ ማለዳ ላይ አውሮፕላን ተሳፍረው ስፍራው ለጊዜው ወዳልታወቀ ቦታ መኮብለላቸውም ነው የተገለጸው።
ከኢድሊብ የተነሳው ሃያት ታህሪር አል-ሻም አማጺ ቡድን ባለፉት ቀናት በአላሳድ ጦር ላይ በከፈተው ጥቃት፥ አሌፖ፣ ሃማ እና ሆምስ የተሰኙ ቁልፍ ከተሞችን መቆጣጠሩ ይታወሳል።
የአማጺ ቡድኑ ግስጋሴውን በመቀጠልም ነው በዛሬው እለት የሶሪያ ርዕሰ መዲናዋን ደማስቆ ከአላሳድ አገዛዝ ነጻ ማውጣቱን ያስታወቀው።
ይህንን ተከትሎም 53 ለሚያህሉ ዓመታት ዘልቆ የቆየው የአባትና ልጅ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱ ነው የተነገረው።
የፕሬዝዳንት በሽል አል አሳድ አባት የሆኑት ሃፌዝ አል አሳድ ሶሪያን ከፈረንጆቹ 1971 አስከ 2000 ድረስ በፕሬዝዳትነት መርተዋል።
ልጃቸው በሽር አላሳድ ደግሞ ከ2000 ጀምሮ ሀገሪቱን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ ዘልቀዋል።