እስራኤል ከ7 የግድያ ሙከራ ያመለጠውን የሀማስ ዋና ወታደራዊ አዛዥ ኢላማ ማድረጓን የጦሩ ራዲዮ አስታወቀ
ዴይፍ በእስራኤል በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተተ ቆይቷል
እስራኤል የጦር አዛዡን ኢላማ አድርጌ ሰንዝሬዋለሁ ባለችው ጥቃት 71 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል
እስራኤል ከ7 የግድያ ሙከራ ያመለጠውን የሀማስ ዋና ወታደራዊ አዛዥ ኢላማ ማድረጓ ተገለጸ።
እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሀማሰን ዋና ወታደራዊ አዛዥ መሀመድ ዴይፍን ኢላማ ማድረጓን የጸጥታ ኃላፊው እና የእስራኤል ጦር ሬዲዮ አስታውቆዋል።
እስራኤል የጦር አዛዡን ኢላማ አድርጌ ሰንዝሬዋለሁ ባለችው ጥቃት 71 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ በጥቃቱ ዴይፍ ስለመገደሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ሬዲዮ እንደገለጸው ዴይፍ እስራኤል የሰብአዊ ቀጣና ብላ በከለለችው ከካን ዮኒስ በምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው አል ማዋሲ በህንጻ ውስጥ ተደብቆ ነበር። ዴይፍ ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ካቀነባበሩት ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታመናል።
ዴይፍ የቅርብ ጊዜውን በፈረንጆቹ 2021 የተፈጸመበትን የግድያ ሙከራ ጨምሮ ከሰባት የእስራኤል የግድያ ሙከራዎች ማምለጥ ችሏል። ዴይፍ በእስራኤል በጥብቅ ከሚፈለጉ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ከተካተተ ቆይቷል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ በዚህ ጥቃት 71 ሰዎች ሲገደሉ 289 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት በጋዛ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታውን በተመለከተ ልዩ ምክክር እንያደረጉ እንደሆነ ቢሯቸው አስታውቋል።
ይህ የአየር ጥቃት በዶሃ እና ኳታር እየተካሄደ ያለውን የእስራኤል እና ሀማስ ድርድር ምን ያህል ተጽእኖ ሊያሳድርበት እንደሚችል አልታወቀም።
በሀማስ የሚመራው ሚዲያ ደግሞ በጥቃቱ የሲቪል ኢንጂነሪንግ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 100 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። የእስራኤል ጦር ይህን ሪፖርት እመለከተዋለሁ ብሏል።
እስራኤል ዴይፍን ኢላማ አድርጌያለሁ ማለቷን "ትርጉም አልባ" ሲሉ የገለጹት የሀማስ ከፍተኛ ባለስልጣን የዴይፍን ደህንነት አላረጋጠጡም።
ባለስልጣኑ አቡ ዙህሪ "ሁለም የተሰውት ንጹሀን ናቸው" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
እስራኤል ዴይፍን የምትፈልገውን ያህል ለሀማስም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይነገራል። የሀማስን የመሬት ውሰጥ ቱቦዎች ኔትወርክ ዲዛይን በማድረግ ስሙ የሚነሳው ዴይፍ፣ በእስራኤል ለተፈጸሙ በደርዘን የሚቆጠሩ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ተጠያቂ ተደርጓል።
የሀማስን የጥቅምት ሰባት ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነ ሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ38ሺ ማለፉን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ተናግረዋል።