እስራኤል የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሀመድ ዴይፍ መገደሉን ማረጋገጧን ገለጸች
ሃማስ የእስራኤልን ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ያመለጠው ዴይፍ ስለመገደሉ እስካሁን አላረጋገጠም
ዴይፍ የአል ቃሳም ብርጌድን በፈረንጆቹ 1990 ከመሰረቱ የሃማስ መሪዎች መካከል አንዱ ነው
የእስራኤል ጦር የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሀመድ ዴይፍ መገደሉን ማረጋገጡን አስታወቀ።
መሀመድ ዴይፍ ከ19 ቀናት በፊት በካን ዩኒስ በተፈጸመ ጥቃት መገደሉን ነው የደህንነት መረጃዎች ማመላከታቸው ነው የተገለጸው።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ፥የዴይፍ ግድያ ሃማስ እየተፈረካከሰ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ሚኒስትሩ “የሃማስ አሸባሪዎች እጅ ይስጡ አልያ ይደመሰሳሉ” የሚል መግለጫም አውጥተዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴርም ሆነ ሃማስ ስለ አልቃሳም ብርጌድ መሪው መሀመድ ዴይፍ ግድያ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።
በፈረንጆቹ ሀምሌ 13 2024 በካን ዩኒስ ዴይፍን ኢላማ ባደረገው ጥቃት ከ90 በላይ ንጹሃን ህይወት መቀጠፉ ይታወሳል።
እስራኤል የሃማስ የፖለቲካ መሪውን ኢስማኤል ሃኒየህ በቴህራን፤ ምክትል የፖለቲካ ሃላፊውን ሳሌህ አል አሩሪ በጥር ወር በቤሩት፤ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪውን መሀመድ ዴይፍ በካን ዩኒስ በመግደል ሃማስን የመደምሰስ ውጥኗን ለማሳካት ጥረት እያደረገች ነው።
ፍልስጤማውያን ግን የሃማስንም ሆነ የሌሎች የፍልስጤም ነጻነት ታጋዮችን አሳዳ ብትገድልም አዳዲስ መሪዎች እየተተኩ ህዝባዊው ትግል ይቀጥላል ሲሉ ይደመጣሉ።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሀመድ ዴይፍ ማን ነበር?
ዴይፍ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ (አል ቃሳም ብርጌድ) በፈረንጆቹ 1990 ከመሰረቱ የሃማስ መሪዎች መካከል አንዱ ነው።
እስራኤል ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የአልቃሳም ብርጌድን ሲመራ የቆየው ዴይፍ ከሃማስ የጋዛ መሪው ያህያ ሲንዋር ጋር በመሆን የጥቅምት 7ቱን ጥቃት እንዳቀነባበረ ታምናለች።
ከሰባት በላይ የእስራኤል የግድያ ሙከራዎችን ያመለጠው ዴይፍ አንድ አይኑን ማጣቱ የሚነገር ሲሆን፥ በአደባባይ ከታየ አመታት ተቆጥረዋል።
“ዴይፍ” በአረብኛ እንግዳ የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን፥ መሀመድ ዴይፍም የእስራኤል የማያቋርጥ የግድያ ሙከራ ለማምለጥ እንደ እንግዳ በየእለቱ አቅጣጫውን ይለውጣል።
አንዳንዶች የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው በእስራኤል ጥቃት በደረሰበት ጉዳት በዊልቼር እንደሚንቀሳቀስ ሲገልጹ ይደመጣል።
በኦንላይን ላይ የሚገኙ የመሀመድ ዴይፍ ምስሎች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን፥ ከእይታ እየተሰወረ ተደጋጋሚ የእስራኤል ጥቃቶችን በማምለጡም “ስውሩ ሰው” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለታል።
እንደ ያህያ ሲንዋር ሁሉ በደቡባዊ ጋዛዋ ካን ዩኒስ በስድተኞች ጣቢያ የተወለደው ዴይፍ በ1980ዎቹ ሃማስን እንደተቀላቀለ ይገመታል።
በ1989 በፍልስጤማውያን “መቅሰፍት” ወይም ኢንቲፋዳ ወቅት በእስራኤል ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ ብዙም ሳይቆይ የተለቀቀው መሀመድ ዴይፍ እስራኤል የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ መሪ ከ22 አመት በፊት ስትገድል ወደ መሪነት መጥቷል።
ሃማስ በጋዛ ረጃጅምና ሰፊ የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻዎችን እንዲገነባ ማገዙና በእስራኤላውያን ላይ ያነጣጠሩ የቦምብ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ማድረጉም ይነገርለታል።
የአልቃሳም ብርጌድ በራሱ አቅም የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን እንዲያመርት በማስቻሉ ረገድም ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ተገልጿል።