እስራኤላውያን ወላጆች ከሞቱ ልጆቻቸው የዘር ፍሬ በመሰብሰብ የልጅ ልጅ እየሳሙ ነው
በጋዛ ጦርነት የሚሳተፉ ወታደር ቤተሰቦች በጦርነቱ ከሚሞቱ ልጆች የዘር ፍሬውን በመውሰድ ለበጎ ፈቃደኛ ሴቶች በመስጠት ነው ልጅ እያስወለዱ ያሉት
ወላጆች ይህን ለማድረግ የፍርድ ቤት ፈቃድ ለማግኝት የሚወስደው ጊዜ እንዳማረራቸው እየተናገሩ ነው
በጋዛው ጦርነት ህይወታቸው የሚያልፍ እስራኤላውያን ወታደር ወላጆች የልጆቻቸውን የዘር ፍሬ በመውሰድ የልጅ ልጅ እያስወለዱ ይገኛሉ፡፡
ወላጆች የልጃቸውን የዘር ፍሬ ከአስክሬኑ ላይ ለመውሰድ የፍርድ ቤት ፍቃድ ለእስራኤል ጦር ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የሟቹን የዘር ፍሬ ለመሸከም ፈቃደኛ የሚሆኑ ሴቶችን በበይነ መረብ እና በተለያዩ መንገዶች እንደሚያፈላልጉ ተሰምቷል፡፡
የዘር ፍሬው ወታደሩ በሞተ በ72 ሰአታት ውስጥ ተወስዶ በማቀዝቀዣ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን ወላጆች የፍርድ ቤት ፈቃድ ማግኝታቸውን የሚያረጋግጥ ወረቀት ባቀረቡ ጊዜ የልጃቸውን የዘር ፍሬ መውሰድ እንደሚችሉ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
የዘር ሀረጋቸውን ለማስቀጠል እና የልጅ ልጅ አቅፎ ለመሳም እንዲሁም የልጃቸውን ምትክ ለማግኝት ይህን አማራጭ የሚጠቀሙ ወላጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሚገኝ ተሰምቷል፡፡
በሃማስ እና እና እሰራኤል መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ 400 የእስራኤል ወታደሮች መሞታቸው ሲገለጽ እስካሁን የ170 የሟች ወታደሮች የዘር ፍሬ መሰብሰቡ ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም ወላጆች በፍርድ ቤት ሟቹ ልጅ የመውለድ ፍላጎት እንዳለው ለማረጋገጥ እና ፈቃድ ለማግኝት የሚወስደው ጊዜ በወራት የሚቆጠር መሆኑ የፈቃድ አሰጣጥ ስርአቱ ቀለል እንዲል በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሰራሩ በእስራኤል የተዋወቀው በ2002 ሲሆን ከሞተ ልጃቸው የዘር ፍሬ በመወሰድ ሴት ልጅ መታቀፍ የቻሉት አያቶች ራሄል እና ያኮቭ ኮሄን ይባላሉ፡፡
ልጃቸው በ2002 በሀማስ ስናይፐሮች የተገደለባቸው ወላጆች ከልጃቸው በወሰዱት የዘር ፍሬ የተወለደችው የልጅ ልጃቸው አሁን ላይ የ10 አመት ታዳጊ ሆናለች፡፡
ኬቨን የተባለው የእስራኤል ወታደር እናት የሆኑት ራሄል ብቸኛ ልጃቸው መሞቱን ተከትሎ በጥልቅ ሀዘን ውስጥ እንደነበሩ ተናግረው የእስራኤል ጦር ያስተዋወቀውን ይህን የልጅ ልጅ የመታቀፍ እድል በመጠቀም የልጄን አምሳያ ማግኝት ችያለሁ ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የፍርድ ቤቱን ፈቀድ ያገኙ ወላጆች የልጃቸውን ታሪክ እና ልጅ ለመውለድ ያለውን ፍላጎት የሚያሳዩ ጽሁፎችን እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በተለያዩ በይነ መረቦች በመልቀቅ ጽንሱን የሚሸከሙ በጎ ፈቃደኛ እናቶችን በማፈላለግ ላይ ናቸው፡፡
ሌሎች ደግሞ በገንዘብ እና በሌሎች ጥቅማጥቅሞች የልጅ ልጅ ለመታቀፍ ሙከራ በማደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡