የሀማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በሃማስ ይዞታ ላይ መጠነሰፊ ጥቃት እያደረሰች ትገኛለች
የእስራእል መንግስት ቻይና የሀማስን ጥቃት አለማውገዟ "ከፍተኛ ቅሬታ" እንደተሰማት ገልጻለች።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቻይና የመካከለኛው ምስራቅ ተወካይ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር የቻይና ሀማስን አለማውገዝ ቅሬታ እንደፈጠረበት ተናግሯል።
ቻይና ያወጣቻቸው መግለጫዎች በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ ሀማስ ያደረሰውን የንጹሃን ጭፍጨፋ እና እገታ እንደማያወግዙ የገለጸው ሚኒስቴሩ በቻይና በእጅጉ ቅር ተሰኝቷል።
አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ሀማስ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል፣ እስራኤል የምትወስደውን የአጸፋ ምላሽ እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
የእስያ ኃያሎቹ ቻይና እና ሩሲያ በአንጻሩ ስለግጭቱ ባወጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ሀማስ ባለፈው ቅዳሜ ባደረሰው ያለተጠበቀ እና ከባድ በተባለው ጥቃት በደቡብ እስራኤል ዘልቆ በመግባት ከ1300 በላይ እስራኤላውያንን ገድሏል።
ጥቃቱን ተከትሎ እስራኤል ጦርነት ውስጥ መግባቷን በማወጅ በሀማስ ላይ መጠነሰፊ የአጸፋ ጥቃት እያደረሰች ተገኛለች።
ሀማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተነሳችው እስራኤል በደቡባዊ እስራኤል ወታደሮቿን በማሰማራት የሀማስ መቀመጫ የሆነችውን ጋዛን በከበባ ውስጥ አስገብታለች።
እስራኤል በሰሜን ጋዛ ያሉ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች በ24 ሰአታት ውስጥ አካባቢያቸውን እንዲለቁ አስጨንቅቃለች።
አለምአቀፍ የሰብአዊ የመብት ተቋማት እና ተመድ ይህን የእስራኤል እቅድ የሰብአዊ መብት ጥስት ያስከትላል በሚል ተቃውመውታል።