ኢራን የአረብ ሀገራት እስራኤልን በጋራ እንዲዋጉ ጠየቀች
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ከሶሪያው አቻቸው በሽር አል አሳድ ጋር ሲመክሩ ነው የትብብር ጥሪውን ያቀረቡት
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በበኩሉ እስራኤል በጋዛ የምትወስደው እርምጃ “የተመጣጠነ” እንዲሆን አሳስቧል
ኢራን ሁሉም ሙስሊም እና የአረብ ሀገራት እስራኤልን በጋራ እንዲዋጉ ጠየቀች።
ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ከሶሪያው አቻቸው በሽር አል አሳድ ጋር በስልክ ሲወያዩ፥
“አሁን ሁሉም የአረብ ሀገራትና ነጻ ህዝቦች እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ወንጀል ማስቆም አለባቸው” ብለዋል።
- የእስራኤል እና የፍልስጤም ሃማስ ጦርነት፤ ምን አዳዲስ ነገሮች ተከስተዋል?
- ሀማስ አሜሪካ "በፍልስጤም ህዝብ ላይ በሚደረገው ወረራ እየተሳተፈች" ነው ሲል ከሰሰ
“እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የምትፈጽመውን ጭፍጨፋ ለማስቆም ኢራን የአረብ ሀገራትን ታስተባብራለች” ማለታቸውንም የኢራን ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በድረገጹ ላይ አስፍሯል።
የፍልስጤሙን ሃማስ በጦር መሳሪያ እና በስልጠና እንደምትደግፍ የሚነገርላት ቴህራን የቅዳሜውን የሃማስ ያልተጠበቀ ጥቃት ብታደንቅም በጥቃቱ ምንም ተሳትፎ የለኝም ብላለች።
የሀገሪቱ መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ የቴህራንን ተሳትፎ ባስተባበሉበት መግለጫቸው፥ “በጺዮናዊው መንግስት ላይ ጥቃት ለማድረስ ያቀዱ አካላትን እጃቸውን እንስማለን” ማለታቸው አይዘነጋም።
የፍልስጤሙ ሃማስ በእስራኤል ላይ የከፈተውን ጦርነት ሶሪያ፣ ሊባኖስ እና ግብጽን ጨምሮ ሌሎች ጎረቤት ሀገራት እንዲቀላቀሉት ጥሪ አቅርቧል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ለሃማስ አጋርነቱን የገለጸ ሲሆን የየመን ታጣቂዎችም እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት በጦርነቱ እጃቸውን እንዳያስገቡ ማሳሰባቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ለእስራኤል አጋርነቷን ለማሳየት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ ቴል አቪቭ የላከችው ዋሽንግተን የጎረቤት ሀገራትን ጣልቃገብነት ለመቀነስ በሚል ግዙፍ የጦር መርከቧን ወደ እስራኤል አስጠግታለች።
በተያያዘ ዜና ለቴልአቪቭ ድጋፋቸውን ለመግለጽ የተሰባሰቡት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት እስራኤል ራሷን የመከላከል ሙሉ መብት እንዳላት የሚያመላክት መግለጫ አውጥተዋል።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ ሃማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን “የሽብር ተግባር” ያወገዙ ሲሆን፥ “እስራኤል ብቻዋን አይደለችም” የሚል መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ይሁን እንጂ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት “የተመጣጠነ” እንዲሆን አሳስቧል።
“ሃማስ ያገታቸውን ንጹሃን በፍጥነት መልቀቅ ይኖርበታል፤ ማንም በዚህ ግጭት ጥቅም ለማግኘት የሚሞክር ሃይል ከድርጊቱ ይታቀብ” ሲልም ነው ኔቶ ያሳሰበው።
እስራኤል 31 አባል ሀገራት ያሉት ኔቶ አባል ባትሆንም የወታደራዊ ጥምረቱ ዋነኛ አጋር መሆኗ ይታወቃል።