ሶስተኛው የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት በሚቀጥለው ሳምንት በካይሮ ይካሄዳል ተብሏል
በእስራኤል ሀማስ ጦርነት ዙሪያ የኢትዮጵያ አቋም ምንድን ነው?
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
የወቅቱ የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት፣ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ውይይት፣ የሱዳን ጦርነት እና ሌሎችም የዲፕሎማሲ ጉዳዮች በመግለጫው ላይ የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
ባሳለፍነው ቅዳሜ በልስጤሙ ሀማስ እና እስራኤል መካከል የተጀመረው ጦርነት የዓለምን ትኩረት የሳበ ሲሆን በርካታ ሀገራት ጦርነቱን ደግፋው እና ተቃውመው መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት ዙሪያ ያላት አቋም ምንድን ነው? ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ላይ ያለው አስተዋጽኦስ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አምባሳደር መለስ ዓለም ምላሽ ሰጥተዋል።
"ኢትዮጵያ በእስራኤል- ፍልስጤም ጉዳይ ዙሪያ ከዚህ በፊት ካላት አቋም የተለየ አቋም አልያዘችም፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት አቋም የሆነው የሁለት ሉዓላዊ ሀገር መሆን ችግሩን ይፈተዋል የሚለው አቋም ትናንትም ሆነ ዛሬም ትክክል እንደሆነ ታምናለች" ብለዋል።
ሌላኛው በዛሬው መግለጫ የተነሳው ጉዳይ ሶስተኛው የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ የባለሙያዎች ውይይት ነው።
አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አለመግባባታቸውን ለመፍታት ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው ብለዋል።
ሁለተኛው የሶስትዮሽ የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ሶስተኛው ውይይት ደግሞ ጥቅምት 11 እና 12 ቀን 2016 ዓ.ም በግብጽ መዲና ካይሮ እንደሚካሄድ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ።
ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስራዎቿን ወደ ቀድሞ አቋሟ መመለሷን የተናገሩት አምባሳደር መለስ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማሻሻል ላይ መሆኗንም አክለዋል።
ኮሎምቢያ፣ ክሮሺያ እና ኒካካራጋዋ በአዲስ አበባ ኢምባሲያቸውን ለመክፈት በይፋ መጠየቃቸው ተገልጿል።
የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያወጣውን የዘር ማጥፋት እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት አስተያየት ትክክል እና ሚዛናዊ አለመሆኑን አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በኢትዮጵያ አቋርጠውት የነበረውን እርዳታ ዳግም በማስጀመር ላይ ናቸው ያሉት አምባሳደር መለስ እርዳታው ለሀገር ውስጥ ድጋፍ ፈላጊዎችም እንዲዳረስ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።