“የሃማስ ብቸኛ አጀንዳ እስራኤልን ማጥፋት ነው” - ብሊንከን
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቴል አቪቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መክረዋል
እስራኤል በጋዛ የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመጀመር ሃማስ ያገታቸውን ሰዎች መልቀቅ ይኖርበታል ብላለች
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለይፋዊ ጉብኝት እስራኤል ገብተዋል።
ሚኒስትሩ በቴልአቪቭ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በሰጡት መግለጫ፥ “የሃማስ ብቸኛው አጀንዳ እስራኤልን ማጥፋትና አይሁዶችን መግደል ነው” ብለዋል።
“ማንኛውም ሰላምና ፍትህ ወዳጅ ወገን የሃማስን የሽብር ተግባር ማውገዝ አለበትም” ነው ያሉት።
እስራኤል ሃማስን ለመግጠም አቅሙ ቢኖራትም የአሜሪካ ድጋፍ እንደማይለያትም አረጋግጠዋል።
ስድስተኛ ቀኑን በያዘው ግጭት እምነት እና ዜግነትን ባልለየ መልኩ በርካቶች መገደላቸውን በማንሳትም፥ በግጭቱ የሞቱ አሜሪካውያን ቁጥር 25 መድረሱን አብራርተዋል።
እስራኤል በምትወስደው የአጻፋ እርምጃ ንጹሃን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባትም ነው ያሳሰቡት።
ብሊንከን በጦርነት ውስጥ ባለችው እስራኤል ያደረጉት ጉብኝት የዋሽንግተን እና ቴልአቪቭ ወዳጅነት ማሳያ ተደርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከፍልስጤም ፕሬዝዳንት ሙሀመድ አባስ ጋር በዮርዳኖስ መዲና አማን በነገው እለት የሚወያዩ ሲሆን፥ በሃማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ንግግር እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በእስራኤል ጉብኝት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የእስራኤል የጦር ምክርቤት “ሃማስን ከምድረገጽ ለማጥፋት” ዝቷል።
በጋዛ የተቋረጡ የውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በሃማስ የተያዙ ከ150 በላይ ሰዎች እስካልተለቀቁ ድረስ ዳግም እንደማይጀመሩ እስራኤል አስታውቃለች።
ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት ጋዛን እያፈራረሳት ነው።
እስራኤል ለምድር ውጊያ እየተሰናዳሁ ነው ማለቷም ከተማዋን ይበልጥ እንዳያፈራርሳት ስጋት ፈጥሯል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የአየር ድብደባ ምክንያት ከ338 ሺህ በላይ ሰዎች ቤት አልባ ሆነው ተፈናቅለዋል።
ስድስተኛ ቀኑን የያዘው እንዲቆም ሃማስ ለንግግር ዝግጁ ነኝ ቢልም እስራኤል “ከአይኤስአይኤስ” ጋር ያመሳሰለችውን የፍልስጤም ቡድን “ለማጥፋት” ዝታ እርምጃ መውሰዷን ቀጥላለች።