እስራኤል ከኢራን ለሚሰነዘርባት ጥቃት የብሪታንያ እና ፈረንሳይን ድጋፍ ጠየቀች
ቴልአቪቭ ከአሜሪካ በተጨማሪ ምዕራባውያን አጋሮቿ ያላቸውን ድጋፍ በግልጽ እንዲያሳዩ ነው የጠየቀችው
የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በትላንትናው እለት በእየሩሳሌም ተገናኝተዋል
እስራኤል ከኢራን ለሚሰነዘርባት ጥቃት እና ለምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ ከአሜሪካ በተጨማሪ ምዕራባውያን አጋሮች ከጎኗ እንዲቆሙ ጠየቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ እስራኤል ካትዝ ከብሪታንያ አቻቸው ዴቪድ ላሚ እና ከፈረንሳዩ ስቴፈን ሰጆርን ጋር በትላንትናው እለት በእየሩሳሌም ተገናኝተው መክረዋል፡፡
በጋዛው ጦርነት ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመፈጸም እንደምትታቀብ አስታወቀች
በውይይታቸው ወቅት እስራኤል ከኢራን የሚሰነዘርባትን ጥቃት ከመከላከል ባለፈ በኢራን ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት ፈረንሳይ እና ብሪታንያ አብረዋት እንዲሚቆሙ በይፋ አቋማቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቃለች፡፡
ይህን ተከትሎ የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ስቴፈን ሰጆርን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራርያ በጋዛው ጦርነት ዙርያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እየተደረገ ባለበት ጊዜ እስራኤል በኢራን ላይ ስለምትፈጽው የአጸፋ ጥቃት መነጋገር ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ከውይይቱ በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫም ከኢራን በተጻራሪ የሚቆም ጥምር ሀይል ስለማቋቋምም ሆነ ከቴልአቪቭ ጎን ተሰልፈው በቴሄራን ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ያሉት ነገር የለም፡፡
በመግለጫቸው ኢራን እና በእርሷ የሚደገፉ ታጣቂዎች ቀጠናውን ወደለየለት ጦርነት ከሚያስገባ ድርጊት እንዲታቀቡ ውጥረቱን ለማረገብ ለሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በጎ ምላሽ እንዲሰጡ ነው የጠየቁት፡፡
የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ድንገቴ ስብሰባ የተደረገው ላለፉት ሁለት ቀናት በሀማስ እና እስራኤል መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሲደረግ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ነው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የሁለት ቀናቱ ድርድር በጎ እርምጃዎች እና መቀራረቦች የታዩበት መሆኑን ገልጸው በመጪው ሳምንት ይቀጥላል ተብሎ የሚጠበቀውን ድርድር ከሚያደናቅፉ ተግባሮች ሁለቱም ወገኖች እንዲሰበሰቡ አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው አንቶኒ ብሊንከንን ወደ እስራኤል በመላክ በድርድር ተግባራዊነት ዙርያ እንደሚመክሩ ተናግረዋል፡፡
ተፋላሚዎቹን ሲያደራድሩ የነበሩት ግብጽ ፣ ኳታር እና አሜሪካ ባወጡት መግለጫ የታጋቾችን መለቀቀቅ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ልዩነቶችን ለማጥበብ የሚረዱ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረባቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
የኢራንን ዛቻ ተከትሎ እስራኤልን ለመከላከል የተለያዩ ምእራባውያን ሀገራት ቃል ገብተዋል ፡፡ እስካሁን ግን ከአሜሪካ በስተቀር ይፋዊ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ እና በጥቃት እና የመከላከል ሂደቱ እንደሚሳተፍ በይፋ ያስታወቀ ሀገር የለም፡፡