ብሪታንያ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትታቀብ ጠየቀች
ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ከኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዚሽኪያን ጋር በጉዳዩ ላይ በስልክ ተወያተዋል
የሀማስ ፖለቲካ ቢሮ ሃላፊ ግድያን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል ላይ ትሰነዝረዋለች ተብሎ የሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ የቀጠናው ውጥረት አባብሷል
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚንስትር ኪር ስታርመር ኢራን በእስራኤል ላይ ለመፈጸም ያሰበችውን የአጸፋ ምላሽ እንድታቆም ጠየቁ፡፡
የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህ በተሄራን መገደሉን ተከትሎ በቴልአቪቭ ላይ ከኢራን ይፈጸማል ተብሎ የሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ እየተጠበቀ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ቀጠናው ወደለየለት ጦርነት ሊመራ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል፡፡
ኪር ስታርመር ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት የአጸፋ ጥቃቱ ከፍተኛ አደጋን የሚያስከትል የጋዛውን ጦርነት ማብቂያም ሊያራዝም የሚችል ሁነት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ እንዲያጤኑበት ጠይቀዋል፡፡
የቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ከቀድሞው የኢራን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሀኒ ጋር በ2021 ካደረጉት የስልክ ንግግር ቀጥሎ ከሶስት አመታት ወዲህ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቀጥታ ሲነጋገሩ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ጀርመን ፣ ፈረንሳይ ፣ ጣሊያን እና አሜሪካ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰነዝር እንድትታቀብ የጋራ መግለጫ ካወጡ በኋላ ሁለቱ መሪዎች ለ30 ደቂቃ የስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡
ምዕራብውያኑ በጋራ ካወጡት መግለጫ ባለፈ እስራል ከኢራን እና በሽብረተኛነት ከተፈረጁ ታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘርባትን ጥቃት መመከት ትችል ዘንድ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የኢራን እና የብሪታንያ መሪዎች በነበራቸው የስልክ ቆይታ ከጋዛው ጦርነት ባለፈ በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ዙርያም መክረዋል፡፡
ለዘብተኛ የሚባሉት አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዚሽኪያን ሀገራቸው ከምእራቡ አለም ጋር የገባችበትን ውጥረት ላማረገብ እና ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው ፕሬዝዳንቱ ከምዕራቡ አለም ጋር ሁኔታዎችን ለማሻሻል ከሚወስዷቸው እርምጃዎች መካከል እስራኤል ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ማስቀረት እንዱ ሊሆን ይችላል፡፡
ሆኖም ውሳኔው ከፕሬዝዳንቱ ባለፈ የሀይማኖታዊ መሪውን አያቶላ አሊ ሀሚኒን ይሁንታ ማግኝት ይኖርበታል፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በእስራኤል ላይ ጥቃት የመሰነዘር እቅድ እንዳልተቀየረ እና በትክክለኛው ሰአት እና ቦታ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጧል፡
አሜሪካ በበኩሏ በቀጠናው ከፍተኛ የጦር መሳርያዎችን እና የውግያ መርከቦችን ያስጠጋች ሲሆን በትላንትናው እለት 154 የቶምሃውክ ክሩስ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፍ የሚችለውን ሰርጓጅ መርከብ ወደ ቀጠናው ልካለች፡፡
ተሄራን በእስራኤል ላይ ምን አይነት ጥቃት ልትሰነዝር እንደምችል ፣ ቦታው እና ጊዜው እስካሁን ባይታወቀም እስራል እና አጋሮቿ ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመጪው ሀሙስ የእስራኤል እና የሀማስ መሪዎች በተኩስ አቁም እና ታጋቾችን በማስለቀቅ ዙርያ በአፋጣኝ እንዲደራደሩ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በድርድሩ በጎ ውጤት የሚገኝ ከሆነ የቀጠናውን ውጥረት በመጠኑም ቢሆን ሊያረግበው እንደሚችል ይጠበቃል