ኢራን እና አጋሮቿ እስራኤል ላይ የጠነከረ ጥቃት ያደርሳሉ በሚል በመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት እንደነገሰ ነው
እስራኤል በአየር ሀይል ወታደሮቿ ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች፡፡
ከ10 ወራት በፊት ሐማስ በእስራኤል ምድር ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡
1 ሺህ 200 ሰዎች በሐማስ ጥቃት ተገድለውብኛል ያለችው እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የድርጅቱ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎችን ገድላለች።
በጋዛ የተጀመረው ይህ ጦርነት በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ወደ ሊባኖስ እና የመን እየተስፋፋ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ በሌሎች አካባቢዎችን ሊሰፋ እንደሚችል ስጋት አይሏል፡፡
በተለይም በኢራን ተመራጩ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ቴህራን ያመሩት የሐማሱ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ መገደል ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል፡፡
ግድያው በግዛቷ የተፈጸመባት ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን እስራኤል መቀጣት እንዳለባት እና እርምጃ እንደምትወስድ ዝታለች፡፡
ሶስት ሀገራት ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እንድትቆጠብ ጠየቁ
እስራኤል ከኢራን፣ ሂዝቦላህ እና በሌሎች ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች አማካኝነት ጥቃት ይደርስብኛል በሚል በተጠንቀቅ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ግብጽ እና ጆርዳንን ጨምሮ ሌሎችም ሀገራት ወደ እስራኤል የሚተኮሱ የአየር ላይ ጥቃቶችን እንደሚያከሽፉ አስቀድመው አስጠንቅቀዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ እስራኤል የአየር ሀይል ወታደሮቿ ወደ ውጪ ሀገራት እንዳይጓዙ ያስጠነቀቀች ሲሆን ወታደሮቹ በኢራን እና አጋሮቿ ኢላማ ሊዳረጉ እንደሚችሉ በመስጋት ነው፡፡
አሜሪካ በበኩሏ እስራኤልን ከጥቃት ለመጠበቅ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን አስቀድማ ወደ ስፍራው የላከች ሲሆን ተጨማሪ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንዲላኩም መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባሳለፍነው ሳምንት ኢራን እና አጋሮቿ በእስራኤል ላይ የተቀናጀ ጥቃታቸውን በሶት ቀናት ውስጥ እንደሚያደርሱ አስጠንቅቆ ነበር፡፡