የእስራኤል ጦር የምድር ኃይል የጋዛ ሰርጥ ዘመቻን ከዛሬ ጀምሮ በስፋት እንደሚያከናውን ገለጸ
ሃማስ፤ እስራኤል ጨማሪ የዘር ፍጅቶችን ለማካሄድ ግንኙነቶችን አቋርጣለች ብሏል
ጦሩ ተጋቾችን ለማስለቀቅና የእስራኤልን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የመድር ዘመቻውን እንደሚያከናውን አስታውቋል
ከ20 ቀናት በፊት ለፍስልጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በአካባቢው የተቀሰቀሰው ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል።
እስካሁን የዓለም ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ የሆነው ይህ ጦርነት መቋጫ ያልተገኘለት ሲሆን በየዕለቱ አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ እና ሰዎች እየተገደሉ እንደሆነ ተገልጿል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ዛሬ ማምሻን በሰጠት መግለጫ፤ የምድር ኃላችን በጋዛ የሚያደርገውን ዘመቻ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ አስፋፍቶ ያካሂዳል ብለዋል።
የጋዛ ነዋሪዎች ከሰሜን የከተማዋ አካባቢ ወደ ደቡብ ለቀው እንዲወጡም ጦሩ አሳስቧል።
“የትግሉን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ በከፍተኛ ኃይል እና በሁሉም ደረጃ እየሰራን ነው” ብሏል የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በመግለጫው።
ጦሩ ተጋቾችን ለማስለቀቅና የእስራኤልን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የመድር ዘመቻውን እንደሚያከናውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል።
ሃማስ በበኩሉ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ፤ እስራኤል ግንኙነት በማቋረጥ ከአየር፣ ከምድር እና ከባሀር የምታደርገውን ጥቃት አጠናክራለች ሲል ከሷል።
የእስራኤል እርምጃ ከዓለም እና ከሚዲያዎች አይን በመሰወር የምትፈጽመውን የጅምላ ግድያ እና የዘር ፍጅት አጠናክራ ለማከናወን ነው ሲልም ከሷል።
የሀማስ ባለስልጣን በጋዛ ታግተው የተወሰዱ ሰዎችን ለመልቀቅ የተኩስ አቁም ያስፈልጋል ብለዋል።