እስራኤል በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ በድጋሚ የታዛቢነት ቦታ ማግኘቷን በኢትዮጵያ የእስራኤል ኢምባሲ አስታወቀ
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ከፈረንጆቹ 2002 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሕብረት የእስራኤል ታዛቢ ሆነው መሾማቸውንም ኤምባሲው አስታውቋ፡፡ ዲፕሎማቱም የታዛቢነት የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንብር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አቅርበዋል፡፡
ዲፕሎማቱ፤ ግንኙነቱ በመደበኛነት መመስረቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል፤ ሽብርተኝነት በአህጉሪቱ እንዳይስፋፋ ለማድረግ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የእስራኤል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ያይር ላፒድ በበኩላቸው ሀገራቸው በአዲስ አበባው ተቋም የታዛቢነት ቦታ ማግኘቷ ከአህጉሩ ጋር ያለው ግንኑነት የሚያድግበት መንገድ መሆኑን መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡ ዕለቱም የእስራኤልና የአፍሪካ ግንኙነት የሚከበርበት መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ከዚህ ባለፈም ለሁለት አስርት ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረው የአፍሪካ እና የእስራኤል ግንኙነት የሚታደስበት እንደሆነም ሚኒስትሩ መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አስታውቀዋል፡፡ ይህ የታዛቢነት ሚናም ቴላቪቭ ከአፍሪካ ጋር ተባብራ እንዲትሰራ ዕድል እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
እስራኤል ወደ ሕብረቱ ታዛቢነት እንድትመለስ የተደረገው በሀገሪቱ እስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ትብብር እና በህብረቱ አባል ሀገራት በሚገኙ የእስራኤል ኤምባሲዎች ጥረት መሆኑም ተገልጿል፡፡