ላለፉት 12 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ኔታንያሁ ዛሬ ስልጣን አስረክበዋል
ናፍታሊ ቤኔት 36ኛው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
የያሚና ፓርቲ መሪው ቤኔት ተሰናባቹን ጠ/ሚ ቤንያሚን ኔታንያሁን በመተካት ነው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ቃለ መሃላ የፈጸሙት፡፡
ያሚናን ጨምሮ፣ የሽ አቲድ እና ብሉ ኤንድ ኋይትን መሰል 8 ፓርቲዎች የፈጠሩት ጥምረት የ49ኝ ዓመቱን ጎልማሳ ለስልጣን አብቅቷል፡፡ ጥምረቱ በእስራኤል ፓርላማ 60 ለ59 በሆነ የ1 ድምጽ ልዩነት በጠባብ ውጤት ነው የጸደቀው።
የያሚና ፓርቲ መሪው ቤኔት እና የሽ አቲድ መሪው ዬይር ላፒድ በጀመሩት የጥምረት መሰረትም መሪዎቹ ለ4 ዓመታት የሚያቆየውን ስልጣን በዙር የሚይዙ ይሆናል፡፡
በዚህም ቤኔት ቀጣዮቹን 2 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለግላሉ፡፡
ዬይር ላፒድ ደግሞ የመጨረሻዎቹን 2 ዓመታት ጠ/ሚ ይሆናሉ፡፡
አዲሱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ማናቸው?
ናፍታሊ መከላከያን ጨምሮ በተለያዩ የሚኒስትርነት ቦታዎች አገልግለዋል።
ላለፉት 12 ዓመታት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉትን ቤንያሚን ኔታንያሁን የሚተኩት ናፍታሊ ከእሩሳሌም እና ቴልአቪቭ በመቀጠል 3ኛዋ ግዙፍ የእስራኤል ከተማ በሆነችው ሃይፋ ነው ከአሜሪካ ካሊፎርኒያ ከመጡ አይሁዶች እ.ኤ.አ በ1972 የተወለዱት፡፡
በእስራኤል ጦር ውስጥ በኮማንደርነት አገልግለዋል፡፡
የህብሩ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሩቅ ሲሆኑም ‘ሳዮታ’ የተሰኘ የመተግበሪያ (ሶፍትዌር) አበልጻጊ ኩባንያ መስርተው ረጅም አመታትን በአሜሪካ አሳልፈዋል፡፡
ወደ እስራኤል ተመልሰውም በወቅቱ ተቃዋሚ የነበረውን ሊኩድ ፓርቲን በመቀላቀል በቤንያሚን ኔታንያ ስር የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ለ2 ዓመታት እስከ 2008 አገልግለዋል፡፡
በ2012 ሃይማኖታዊውን የይሁዲ (Zionist Bayit Yehudi) ፓርቲ እየመሩ በ2013ቱ ምርጫ ወደ ሃገሪቱ ተወካዮች ምክር ቤት (ክኔሴት) ለመግባት የቻሉ የፓርቲው መሪም ናቸው፡፡
ይህ በፓርቲው ታሪክ ከ36 ዓመታት ወዲህ የሆነ ነው፡፡
ከዚያም ወዲህ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖታዊ ጉዳዮች፣ የዳያስፖራ፣ የትምህርት እና የመከላከያ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡
አሁን ደግሞ ከተለያዩ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የኔታንያሁን ስልጣን የነቀነቀ ተተኪ መንግስትን ለመፍጠር ችለዋል፡፡
ጥምረቱ በፓርቲያቸው ያሚና እና በዬይር ላፒድ በሚመራው የሽ አቲድ ፓርቲ መካከል የተጀመረ ነው፡
ኋላ ላይም የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ አጣማሪን ብሉ ኤንድ ኃይትን ጨምሮ በቀድሞው የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር አቪግዶር ሊበርማን የሚመራውን የስራዬል በይተኑ ፓርቲን ያካተተ ጠንካራ የ8 ፓርቲዎች ጥምረት ለመፍጠር ተችሏል፡፡
ዛሬ የተሰበሰበው ክኔሴት ጥምረቱ ቀጣዩ የሃገሪቱ ስልጣን ተረካቢ መሆኑን አጸድቋል፡፡
በተጣማሪ ፓርቲዎቹ ስምምነት መሰረትም ፖለቲከኞቹ ለ4 ዓመታት የሚያቆየውን ስልጣን በዙር የሚይዙ ይሆናል፡፡
በዚህም ቤኔት ቀጣዮቹን 2 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያገለግሉ ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንደሚቆዩ የተነገረላቸው ዬይር ላፒድ ደግሞ ቀሪዎቹን 2 ዓመታት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡