እስራኤልና የፍልስጤሙ ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ደስታቸውን እገለጹ ነው
ሁለቱ ወገኖች ከዛሬ ጀምሮ የተኩስ አቁም ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን፤ ሁለቱም አሸናፊ ነን እያሉ ነው
እስራኤል እና የፍልስጤሙ ሀማስ ትናንት ምሽት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ 11 ቀናትን ካስቆጠረው የእሰራኤል ሀማስ ግጭት በኋላ ዛሬ ማለዳ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ተነግሯል።
የተኩስ አቁም ስምመነት ላይ ከመደረሱ በፊት ትናንት ምሽት እስራኤል በጋዛ ከ100 በላይ የሀማስ ኢላማዎችን የደበደበች ሲሆን፤ ሀማስ በአጸፋው ሮኬቶችን ወደ አስራኤል መተኮሱ ተሰምቷል።
ሆኖም ግን ሁለቱም ወገኖች ከዛሬ ጠዋት ጀምረው የተኩስ አቁም ለማድረግ ከስምምነት የደረሱ ሲሆን፤ እስራኤል እና የፍልስጤሙ ሀማስ ራሳቸውን አሸናፊ ነን እያሉ ነው።
ሁለቱ ወገኖች ስለ ተኩስ አቁሙ ምን አሉ?
የእስራኤል ፖለቲካዊ የደህንነት ካቢኔ የተኩስ አቁም ጥያቅውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበሉን ያስታወቀ ሲሆን ፣ በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ የዘመቻውን ቀጣይነት የሚወስን ይሆናል ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝም በትዊተር ገጻቻው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ፣ በጋዛ የወሰዱት እርምጃ ያልተጠበቁ ወታደራዊ ድሎች የተመዘገቡበት ነው ብለዋል።
የሀማስ ባለስልጣናት በበኩላቸው በአሁኑ ግጭት ፍልስጤማውያን ማሸነፋቸውን እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ መሸነፋቸውን ያስታወቀ ሲሆን፤ አሁንም ቢሆን ግን እጃቸው በመሳሪያ ቃታ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ መውጣታቸውም ነው ተነገረው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ እና የብሪታኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
እስራኤል እና በጋዛ የሚንቀሳቀሰው ሀማስ ግጭት ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ በ11 ቀን ቆታው በሁለቱም ወገን የበርካቶችን ህይወት ለህልፈት ዳርጓል።
በፍልስጤም በኩል ቢያንስ የ232 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 65 ህጻናት እና 35 ሴቶች ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከ1 ሺህ 500 በላይ ፍልስቴማውያን ደግሞ መቁሰላቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
በእስራኤል በኩል ደግሞ የ12 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 2 ህጻናት ናቸው፤ ከ300 በላይ አስራኤላውያን ደግሞ ቆስለዋል።
በ11 የግጭቱ ቀናት ውስጥ ጋዛ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሀማስ ከ4 ሺህ በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል የተለያዩ ከተሞች መተኮሱን እስራኤል አስታውቃለች።
እስራኤልም በቀን በአማካኝ አስከ 100 የሚደርሱ የአየር ድብደባዎችን በጋዛ ሰርጥ ስትፈጽም የቆየች ሲሆን፤ ወደ ሊባስም ከ100 በላይ መድፎችን መተኮሷ አይዘነጋም።