የተቃዋሚዎቹ ጥምር ስምምነት ኔታንያሁን ከስልጣን ለማውረድ የሚያስችል ነው
የእስራኤል ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስት ለመመስረት ከስምምነት ደረሱ፡፡
የተቃዋሚዎቹ ስምምነት በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በጣም ረጅም ጊዜ ያገለገሉና የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ቀኝ-ዘመምነት እንዲያጋድል አድርገዋል የተባሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከስልጣን ለማውረድ የሚያስችል እንደሆነ ዚ-ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
በፓርቲዎቹ የተላለፈው መግለጫ እንደሚለው ከሆነ ስምምነቱ “በሁለት ዓመታት ውስጥ አራት ምርጫዎችን ላደረገችው፣ የተረጋጋ መንግስትም ሆነ የክልል በጀት ባለመኖሩ የፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ ለቆየችው እስራኤል ያላትን ሸክም የሚያቀል ነው” ተብሎለታል ፡፡
አዲሱ ጥምረት ያልተለመደና ከግራ ወደ ቀኝ የቀረቡ የተለያዩ አመለካከቶች ያሏቸው ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀፈ ነው፡፡
በእስራኤል ታሪክ ቀኝ ዘመም ነው የሚባልለት “ራአም” የተሰኘ የዓረብ ፓርቲዎች ጥምረት (United Arab List) ም የስምምነቱ አካል ሆኗል፡፡
አንዳንድ ተንታኞች ቅንጅቱ የወቅቱን ህብረተሰብ የአስተሳሰብ አድማስ እና ውስብስብነት የሚያንፀባርቅ ነው ብለው ሲያወዱሱት፤ ሌሎች ደግሞ አባላቱ የማይጣጣሙና ሆድና ጀርባ ናቸው፤ እናም ጥምረቱ የእስራኤልን የፖለቲካ ውድቀት ሁነኛ ማሳያ ነው በማለት ሲተቹ ተደምጠዋል፡፡
ጥምረቱ እስከ ጎርጎሮሳያውያኑ 2023፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቀኝ እጅ በመባል ይታወቁ በነበሩት በቀድሞው የእስራኤል ጦር አዛዥ ናፍታሊ ቤኔት ይመራልም ነው የተባለው፡፡
በተቃዋሚዎቹ ስምምነት መሰረት የያሚና ፓርቲ መሪው ናፍታሊ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓመታት የየሽ አቲድ ፓርቲ መሪው ዬይር ላፒድ ደግሞ የመጨረሻዎቹን 2 ዓመታት እስራኤልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚያስተዳድሩ ይሆናል፡፡
ተስማምተው ጥምር መንግስት ለመመስረት መዘጋጀታቸውንም ተቃዋሚዎቹ በቀጣዩ ወር ስልጣን ለሚለቁት ለፕሬዝዳንት ሩቨን ሪቭሊን ትናንት ቀነ ገደቡ ከማጠናቀቁ ከሰዓታት በፊት አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም ስምምነቱ በመጪው ሳምንት እንደሚሰበሰብ በሚጠበቀው የተወካዮች ምክር ቤት (ክኔሴት) መጽደቅ አለበት፡፡
ይህ የሚሆን ከሆነ እስራኤልን ለ12 ዓመታት ያገለገሉት የጠ/ሚ ኔታንያሁ የስልጣን ዘመን የሚያበቃ ይሆናል፡፡