እስራኤልና ሃማስ ታጋቾች እና እስረኞችን እንዴት ነው የሚለዋወጡት?
ለ42 ቀናት የሚቆየው የመጀመሪያው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ከሶስት ስአት መዘግየት በኋላ ተፈጻሚ መሆን ጀምሯል
ሃማስ 33 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ከ1 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትፈታለች
እስራኤልና ሃማስ የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ጠዋት ላይ መተግበር መጀመር ቢኖርም ሃማስ የሚለቀቁ ታጋቾችን ስም ዝርዝር ለእስራኤል በፍጥነት ባለመላኩ ለሶስት ስአታት ዘግይቷል።
ከአንድ ስአት በፊት ተፈጻሚ መሆን የጀመረው የተኩስ አቁም ለ15 ወራት በጦርነት ለከረመችው ጋዛ እፎይታ ይሰጣል ተብሎ ታምኖበታል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ፤ የታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞች አለቃቀቅ
የእስራኤል እና ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነት በሶስት ምዕራፍ የተከፋፈለ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ ለ42 ቀናት የሚቆይ ሲሆን 33 ታጋቾች በሰባት ዙሮች ይለቀቁበታል።
ሃማስ አንድ እስራኤላዊ ሲቪል ታጋች ሲለቅ እስራኤል በምትኩ 30 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።
የሚለቀቀው/የምትለቀቀው ታጋች ወታደር ከሆነ/ች ደግሞ እስራኤል 30 የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸውና 20 ረጅም አመታትን በእስር ያሳለፉ በድምሩ 50 ፍልስጤማያን እስረኞች ይለቀቃሉ።
የሚለቀቁ ታጋቾች
የመጀመሪያ ቀን (ዛሬ) - 3
ሰባተኛ ቀን - 4
14ኛ ቀን - 3
21ኛ ቀን - 3
28ኛ ቀን - 3
35ኛ ቀን - 3
የመጨረሻ ሳምንት - 11
እስራኤል በወቅታዊው የተኩስ አቁም ስምምነት 1890 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትለቅ ተገልጿል።
ከእስራኤል እስርቤቶች የሚለቀቁ ፍልስጤማውያን ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ስር በዋሉበት ምክንያት ዳግም አይታሰሩም፤ ከእስርቤት ለመውጣት ምንም አይነት ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ማኖር አይጠበቅባቸውም ተብሏል።
ለስድስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያው ምዕራፍ ተኩስ አቁም እስራኤል ወታደሮቿን ህዝብ ከሚበዛባቸው የጋዛ ከተሞች ቀስ በቀስ ታስወጣለች፤ ፍልስጤማውያንም ወደ ቀያቸው መመለስ ይጀመራሉ።
በስምምነቱ መሰረት በየቀኑ 600 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች፤ 50 የነዳጅ ቦቴዎች ወደ ጋዛ ይገባሉ።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ከተጀመረ ከ16 ቀናት በኋላ የሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ነጥቦች ላይ ድርድር ማድረግ ይጀመራል።
ይህ ምዕራፍ ቀሪ ታጋቾችን (ወንዶችና ወታደሮች) የሚለቀቁበትንና የእስራኤል ወታደሮችን ሙሉ በሙሉ ከጋዛ የሚወጡበትን ሂደት የሚይዝ ነው። የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ የሞቱ ታጋቾችን አስከሬን መመለስና የፈራረሰችውን ጋዛ ዳግም መገንባት ላይ ያተኩራል።