የእስራኤል ካቢኔ የጋዛውን ተኩስ አቁም ስምምነት አጸደቀ
ለቀናት ሲጠበቅ የነበረው የጋዛውን ተኩስ አቁም እውን የሚያደርገው ስምምነት በ24 ድጋፍ በ8 ተቃውሞ ጸድቋል
ስምምነቱ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደርግ ቢጠበቅም እስራኤል ዛሬ ንጋት ድረስ በጋዛ የምታደርገውን ጥቃት አላቆመችም
15 ወራቱ ያቆጠረውን የእስራኤል እና ሀማስ ታጣቂዎች የጋዛ ጦርነት ያስቆማል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት በእስራኤል ካቢኔ ጸደቀ፡፡
በትላንትናው ዕለት የተሰበሰበው የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ 32 አባላትን ለያዘው ሙሉ ካቢኔ ስምምነቱ ለመጽደቅ ከመቅረቡ በፊት ረጅም ጊዜ የወሰደ ውይይትን አድርጓል፡፡
ለ6 ሰአታት ከፈጀው የደህንነት ካቢኔ ውይይት በኋላ የቀረበው ስምምነት በ24 ድጋፍ እና በ8 ተቃውሞ ተግባራዊ መሆን የሚያስችለውን ድጋፍ አግኝቷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ እና የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው በእስራኤል ጥምር መንግስት ውስጥ ስምምነቱን አጥበቀው ከተቃወሙ የካቤኔ አባላቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተለይም የገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች የመጀመሪያው የስድስት ሳምንት የተኩስ አቁም ምዕራፍ ከጠጠናቀቀ በኋላ ሃማስን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት መንግስት ወደ ጦርነት ካልተመለሰ ከሀላፊነታቸው እንደሚለቁ ዝተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ባወጣው አጭር መግለጫ ታጋቾች የሚመለሱበትን እና የጋዛው ጦርነት የሚቆምበትን የተኩስ አቁም ስምምነት መንግስት አጽድቋል ሲል አስታውቋል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰበት ረቡዕ ጀምሮ በጋዛ የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ከፍተኛ ጥቃቶችን ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።
ምንም እንኳን ስምምነቱ ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ቢጠበቅም ቅዳሜ ማለዳ የእስራኤል የአየር ጥቃት ከካን ዮኒስ በስተ ምዕራብ በሚገኘው ማዋሲ አካባቢ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ አምስት ሰዎችን መግደሉን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ይህም ስምምነቱ በኳታር ተደራዳሪዎች ከተፈረመ በኋላ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉትን ፍልስጤማውያን ቁጥር 119 አድርሷል።
ካቢኔው ስምምነቱን ካፀደቀ በኋላ የአሜሪካ መሪ ተደራዳሪ ብሬት ማክጉርክ እቅዱ ወደ ፊት እየሄደ መሆኑን ተናግረው፤ እሁድ ከሰአት በኋላ በሀማስ ስር የሚገኙ 3 ሴት ታጋቾች በቀይ መስቀል በኩል ወደ እስራኤል እንደሚላኩ ገልጸዋል፡፡
በሶስት ምዕራፎች የሚተገበረው የተኩስ አቁም የሚጀምረው በመጀመሪያ የስድስት ሳምንት ምዕራፍ ሲሆን በሃማስ የተያዙ ታጋቾች በእስራኤል በታሰሩ እስረኞች ልውውጥ ይደረጋል፡፡
ከ98ቱ ቀሪ እስራኤላውያን ታጋቾች መካከል 33ቱ ሴቶች፣ ህጻናት እና እድሜቸው ከ50 በላይ የሆኑ ሰዎችን ጨምሮ በዚህ ምዕራፍ ነጻ ይወጣሉ።
እስራኤል በበኩሏ በእስር ቤቶች የሚገኙ ከ19 አመት በታች የሆኑ ፍልስጤማውያን ሴቶች እና ህጻናትን በሙሉ በመጀመሪያው ምዕራፍ መጨረሻ ትፈታለች።
በነገው ዕለት ሶስት ተጋቾች ከሀማስ ሲለቀቁ በተመሳሳይ ቀን እስራኤል 95 እስረኞችን የምትለቅ ይሆናል፡፡
ቀጥሎም ስምምነቱ 4 ተጨማሪ ሴት ታጋቾች ከሰባት ቀናት በኋላ እንዲለቀቁ ያስቀመጠ ሲሆን ከዛም በየሰባት ቀናት ልዩነት ውስጥ ተጨማሪ ሶስት ታጋቾች የሚለቀቁ ይሆናል፡፡