ሃማስ የታጋቾችን ዝርዝር ይፋ ካላደረገ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መተግበር አይጀምርም - ኔታንያሁ
ተጠባቂው የተኩስ አቁም ከመጀመሩ ከአንድ ስአት በፊት በእስራኤል እና ጋዛ ድንበር የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል
የፍልስጤሙ ሃማስ በበኩሉ የታጋቾቹን ስም ይፋ ያላደረገው "በቴክኒካዊ ምክንያቶች" መሆኑን ጠቅሶ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል
እስራኤል እና ሃማስ በጋዛ ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ መፈጸም ከመጀመሩ ከአንድ ስአት በፊት ግን በእስራኤልና ጋዛ ድንበር የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ሬውተርስ ዘግቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው ሃማስ የታጋቾችን ስም ዝርዝር ይፋ ካላደረገ ተኩስ አናቆምም ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት በሚገባ ካልተፈጸመ እስራኤል በሃማስ ላይ ዳግም ጦርነት እንደምትከፍትም ዝተዋል።
የሃማስ መሪዎችን በመግደል "የመካከለኛው ምስራቅ መልክን ቀይረናል" ያሉት ኔታንያሁ፥ በ15 ወራቱ ጦርነት "ሃማስን ብቻውን አስቀርተነዋል" ማለታቸውንም ቢቢሲ አስነብቧል።
እስራኤል በአሜሪካ፣ ኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት አፈጻጸም መጣስ በፍጹም እንደማትታገስና ሃማስ የታጋቾችን ስም ይፋ ካላደረገ ተኩስ እንደማይቆምም ገልጸዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በሃማስ የሚለቀቁትን 33 ታጋቾች ስም ዝርዝር ይፋ ቢያደርጉም በሀገሪቱ ባለስልጣናት ማረጋገጫ አልተሰጠውም።
የፍልስጤሙ ሃማስ የታጋቾቹን ስም ይፋ ለማድረግ የዘገየው "በቴክኒካዊ ምክንያቶች" መሆኑን ጠቅሶ ለስምምነቱ ተፈጻሚነት ቁርጠኛ መሆኑን መግለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሰረት ሃማስ ዛሬ ሶስት ታጋቾችን ይለቃል። እስራኤልም 30 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንደምትፈታ ይጠበቃል።
በሶስት ምዕራፍ ተግባራዊ በሚደረገው ስምምነት ሃማስ 33 ታጋቾችን፤ እስራኤል ደግሞ 1890 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ይለቃሉ።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዛሬው እለት ሃማስ የሚለቃቸው ታጋቾች ሴቶች መሆናቸውን የዘገበ ሲሆን፥ በሰሜናዊ፣ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ጋዛ ታጋቾችን መቀበያ ስፍራዎች መዘጋጀታቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
47 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት ቆሞ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተፈጻሚነት አጥብቀው ይሹታል።
ከአንድ አመት በላይ ይቺን ቀን ሲጠባበቁ የቆዩ የታጋቾች ቤተሰቦችም የስምምነቱን መተግበር እንጂ መጣስ አይሹም።