በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን ዱለሳ ወረዳ ባጋጠመው ርዕደ መሬት 18 ትምህርት ቤቶች መፍረሳቸው ተነገረ
በአካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከተለዩ የማህበረሰብ ክፍሎች 97 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሌላ ቦታ መስፈራቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል
በአፋር ክልል ያለ ማቋረጥ የመሬት መንቀጥቀጥ ብርቱ ሆኖ ከሚሰማባቸው ስፍራዎች መካከል ገቢ ረሱ ዞን ዱለሳ ወረዳ ነው
ከባለፈው መስከረም ጀምሮ በኢትዮጵያ በአፋር ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየተስተናገደ የሚገኝው ርዕደ መሬት አሁንም አልቆመም፡፡
ለመሬት መንቀጥቀጥ መነሻ ናቸው በሚባሉት የፈንታሌ እና ዶፋን ተራሮች አቅራቢያ በሚገኙ አካባቢዎች በሰዓታት አንዳንዴም በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ንዝረቶችን ይስተናግዳሉ።
በዞኑ እስካሁን ከተከሰቱ ርዕደ መሬቶች በሬክተር ስኬል ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው 5.2 የተሻገረው ሲሆን በዚህም የመሬት መሰንጠቅ ፣ የመኖርያ ቤቶች እና ህንጻዎች መፍረስ እንዲሁም በሌሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል፡፡
ላለፉት ሳምንታት በአፋር ክልል ያለ ማቋረጥ የቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ ብርቱ ሆኖ ከሚሰማባቸው ስፍራዎች መካከል ገቢ ረሱ ዞን ዱለሳ ወረዳ ይጠቀሳል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ አብዱ አሊ የመሬት መንቀጥቀጡ ከመስከረም ወር ጀምሮ መታየት ቢጀምርም በዋናነት ከታሕሳስ 10 ጀምሮ መጠኑ ቢለያይም በአዋሽ ፈንታሌ እና ዱለሳ ወረዳ ላይ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬቶች መከሰታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት ከዱለሳ ሁለት ቀበሌዎች ከአዋሽ ፈንታሌ ደግሞ የ5 ቀበሌ ነዋሪዎች በአጠቃላይ ከ9 ሺህ በላይ አባወራዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ የዞኑ አስተዳደሪ ተናግረዋል፡፡
እስካሁን በተፈጠሩት ርዕደ መሬቶች የመንግስት ተቋማት ፣ የእርሻ ማሳዎች ፣ መስጂዶች ፣ ጤና ኬላ ፣ መኖርያ ቤቶች ፣ የንግድ ሱቆች ፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የሚናገሩት አቶ አብዱ በሰው እና እንስሳት ላይ በሁለቱም ወረዳዎች ጉዳት አለመመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በአዋሽ ፈንታሌ ቀበና ከተማ የሚገኝው የከሰም ስኳር ፋብሪካ በአካባቢው በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገዱ ተቋማት መካከል አንዱ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የዱለሳ ወረዳ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አሊ ሁሴን በወረዳው ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገዱ መሰረተ ልማቶች መካከል የትምህርት ተቋማት ቀዳሚዎቹ እንደሆኑ ያነሳሉ፡፡
“እስካሁን በአጠቃላይ 18 ትምህርት ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 6 ሙሉ ለሙሉ የፈረሱ ናቸው፤ የአደጋው ቀጣይነት እና ተፈናቃዮች ወደ አከባቢያቸው የሚመለሱበት ቀን ስለማይታወቅ በተፈናቃይ መጠለያዎች ውስጥ ትምህርት ለማስቀጠል ከክልል ትምህርት ቢሮ ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተፈናቃዮች ሁኔታን በተመለከተ ከ6 ቀበሌዎች ከ9 ሺህ በላይ አባወራዎችን ከስፍራው ማስነሳት መቻሉን ነው የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱ አሊ የሚናገሩት፡፡
“በአሁኑ ወቅት የዱለሳ ወረዳ ሙሉ ለሙሉ ለኑሮ ምቹ ባለመሆኑ ከአካባቢው ሰዎችን ወደ ሌላ ስፍራ የማስፈር ስራ እየሰራን ነው፤ መንግስት ሰዎችን ወደ ሌላ ስፍራ ማጓጓዝ ሳይጀምር ቀደም ብለው በራሳቸው አካባቢውን ለቀው የወጡ አሉ፤ እኛ ማስወጣት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ግን ዳይኢዶ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተፈናቃይ ጣብያዎችን በማቋቋም የ6 ቀበሌ ነዋሪዎችን በእዛው እንዲሰፍሩ አድርገናል” ነውያሉት፡፡
እሁድ ታህሳስ 27 እና ሰኞ ታህሳስ 28 ጀምሮ በነዚህ መጠለያ ጣብያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች መሰረታዊ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት ከአደጋ መከላከል ኮሚሽን እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ መደረግ መጀመሩን አቶ አብዱ አክለው ገልጸዋል፡፡
የፌደራል የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ በዱለሳ ወረዳ 20 ሺህ ነዋሪዎች ለርዕደ መሬት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጾ ነበር፡፡
ዳይኢዶ ከተባለው ስፍራ ባለፈ በሌሎች ሁለት የተፈናቃይ ጣብያዎች ዜጎች መስፈራቸውን የተናገሩት በአፋር ክልል የገቢ ረሱ ዞን አስተዳዳሪ እስካሁን ባለው 97 በመቶ ነዋሪዎችን ከስጋት ቀጠና አካባቢዎች ማስወጣት መቻሉን አመላክተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ረብዕ እና ሀሙስ የመሬት መንቀጥቀጡ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ሲሆን አርብ እና ቅዳሜ ደግሞ ጠንከር ያሉ ርዕደ መሬቶች መስተናገዳቸውን የዞኑ አስተዳዳሪ ያነሳሉ፡፡
አቶ ሰኢድ ያሲን ከዱለሳ ወረዳ ተፈናቅለው በዳይኢዶ መጠለያ ጣብያ ውስጥ የሚገኙ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው እሳቸው ስለ መሬት መንቀጥቀጡ ሲናገሩ “ከታህሳስ ወር ጀምሮ ሌሊት ላይ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ አስጨናቂ የመሬት መንቀጥቀጥ እንሰማ ነበር፤ ቀን ቀን ደግሞ በቆምንበት መሬት ሲሰነጠቅ መኖሪያ ቤቶች ሱፈርሱ ተመልክተናል። ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ነገር አይተን አናውቅም” ብለዋል፡፡
ሌላላኛው አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው ወግሪስ መሀመድ የተባሉ ነዋሪ እንዳሉት ደግሞ “መንቀጥቀጡ አንዳንድ ጊዜ ዝቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከፍ ይላል፤ ሌሊት በተኛንበት የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ብለን ቁጭ ብለን ያርንበት ጊዜ ብዙ ነው፤ ውጭ ለመተኛት ስንሞክርም ቤቱ እላያችን ላይ እንዳይፈርስ ያግዛል እንጂ ጭንቀቱ ተመሳሳይ ነው፤ አሁን በምንገኝበት ሁኔታ ተማሪዎች ከትምህርትታቸው እኛም ከስራችን ከመስተጓጎላችን በስተቀር የምግብ ድጋፍ እየቀረበልን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አቶ ወግሪስ ፍል ውሀ እና እሳተ ጎመራ መሰል ፍንዳታዎች ከተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚመጣው መጥፎ ሽታም የሚስቀምጥ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦስፓሻል እና የስነ መሬት ተመራማሪዎች በአካባቢው ወደ ላይ የሚፈነዳው ውሃ ከፍተኛ ሙቀት ያለው፣ ሰልፈር ዳይኦክሳይድና ሌሎች መርዛማ ጋዞችን የያዘ በመሆኑ ለሰው ልጆች ጤና አደገኛ ስለመሆኑ አሳስበዋል፡፡
የተፈናቃዮች ቀጣይ እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን? በአካባቢው ያለውን ሁኔታ መፍትሄ ለመድረስ ምን እየተሰራ እንደሆነ የጠየቅናቸው ገቢ ረሱ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱ፤ ከአዲስ አበባ ፣ ከአዳማ እና ከሰመራ ዩኒቨርስቲዮች የተውጣጡ ጂኦሎጂስቶች እሳተ ጎመራ መሰል ፍንዳታ በተከሰተባቸው እና መሬት ውስጥ እንቅስቃሴ አለባቸው በሚባሉ ከአዋሽ ፈንታሌ ወደ ዶፈን ተራራ በሚወስደው መስመር ላይ በአሁኑ ወቅት ጥናት እያደረጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
ከጥናቱ ውጤት በኋላ ቀጣይ እርምጃዎችን ለመወሰን ውይይት ይደረጋልም ተብሏል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከክልል መንግስት ፣ ከፌደራል አደጋ ስጋት እና ስራ አመራ ኮሚሽን የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አብዱ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ ድጋፍ ሊያስፈልግ እንደሚችል ገልጸዋል