እስራኤል በሊባኖስ በእግረኛ ጦር ዘመቻ ጀምራለች፤ ሄዝቦላህ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል እየተኮሰ ነው
በሊባኖስ የመገናኛ መሳርያዎች ላይ የተገጠሙ ፈንጂዎችን በማፈንዳት ጥቃት ማድረስ የጀመረችው እስራኤል ካሳለፍነው ሳምንት ሰኞ ጀምሮ መጠኑ ከፍ ያለ የአየር እና የሚሳኤል ጥቃት በሊባኖስ ላይ እየፈጸመች ትገኛለች።
ሄዝቦላህ ለእስራኤል እየሰጠ በሚገኝው ምላሽ እስከዛሬ በቡድኑ ጥቅም ላይ ውለው የማያውቁ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ጭምር በመጠቀም በማዕከላዊ እስራኤል ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል።
ምን አዳዲስ ክስተቶች ተስተናግደዋል?
-የእስረኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ እግረኛ ጦሩን በማስገባት የምድር ለምድር ውጊያ መጀመሩን አስታውቋል።
-በሊባኖስ የተለያዩ ክፍሎች ላይ የሚፈጸመው የእስራኤል የአየር ድብደባም የቀጠለ ሲሆን፤ በዳውዲያ በተፈጸመ ጥቃት 10 ሰዎች ሞተዋል።
- ሊባኖስ ውስጥ የሚገኘው የፍሊስጤሙ ፋታህ- አላስቃ ሰማእታት ብርጌድ አዛዥ ሙኒር አል ማቅዳህ ቤት በአየር የተደበደበ ሲሆን፤ በዚህም 5 ሰዎች ሞተዋል።
- የሊባኖስ ሚዲያዎች ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ አዛዡ ሙኒር አል ማቅዳህ ከእስራኤል የግድያ ሙከራ ማምልጥ ችሏል፤ የአል ማቅዳህ ወንድ ልጅ ግን በጥቃቱ ተገድሏል።
እስራኤል በአጠቃላይ ትናንት ሰኞ በመላው ሊባኖስ ባካሄደችው ድብደባ 95 ሰዎች ሲሞቱ፤ ከ172 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የሄዝቦላህ ሮኬት ወደ እስራኤል
-ሄዝቦላህ በታናንትናው እለት ከ10 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል የተኮሰ ሲሆን፤ ሮኬቶችም በሰሜናዊ እስራኤል የምትገኘውን ሜሮንን እና አካባውን ኢላማ ያደረገ ነው።
-የእስራኤል ጦር ከሮኬቶቹ አብዛኛውን ማክሸፉን እና የተወሰኑት ግን አምልጠው መሬት ላይ መውደቃቸውን ገልጾ፤ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል።
ሄዝቦላህ ዛሬ ጠዋት ላይም ሶሰት ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል፤ እስራኤል ከተተኮሱት ሮኬቶች ሁለቱን ማከሸፉን እና አነዱ አልፎ መሬት ላይ ማረፉን አስታውቋል።
የእስራኤል- ሄዝቦላህ ግጭት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ
የእስራኤል ጥቃት በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ስጋትን እና ውጥረትን የፈጠረ ሲሆን፤ በደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።
የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ፤ እስከ አንድ ሚሊየን የሚደርሱ ሊባኖሳውያን ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።
የተባሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ ፊሊፖ ግራንዲ፤ በሊባኖስ ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸውን አስታውቀው፤ ከ50 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገር ሶሪያ መሰደዳቸውን አስታውቀዋል።
ከ70 ሺህ በላይ እስራኤላውያንም በሄዝቦላህ እና እስራኤል ድንበር ላይ የተኩስ ለውውጥ ከተጀመረ ወዲህ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል።