የእስራኤል ጦር ትናንት ምሽቱን ወደ ሰሜን ጋዛ መግበቱን እና አሁንም በዚያው እንደሚገኝ አስታውቋል
የእስራኤል ጦር ትናንት ምሽቱን ወደ ሰሜን ጋዛ መግበቱን እና አሁንም በዚያው እንደሚገኝ አስታውቋል።
ጦሩ እንደገለጸው ሰሜን ጋዛ ገብቶ በእግረኛ ጦር እና በብረት ለበስ ይዞታውን እያሰፋ እንደሚገኝ ተናግሯል።
የጦር ቃል አቀባይ ዳንኤል ሀጋሪ የእስራኤል ኃይሎች አሁንም "መሬት ላይ ናቸው" በማለት ያልተብራራ መልስ ሰጥተዋል።
ሀጋሪ የሰብአዊ እርዳታውን ማስፋታቸውን እና ምግብ እና ውሃ የያዙ ተሽከርካሪዎች ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲገቡ እንደሚፈቀድላቸው ተናግረዋል።
የእስራኤል ጦር ሌሊቱን ባካሄደው ዘመቻ የሀማስን የባህር እና የአየር ኃይል አዛዦችን መምታቱን የገለጹት ቃል አቀባይ ይህ ጦሩ "ከደካማ ኃይል" ጋር እንዲዋጋ ያስችለዋል ብለዋል።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው ጉባኤ በጋዛ ለሰብአዊ እርዳታ የሚሆን ተኩስ አቁም እንዲደረግ በአብላጫ ድሞጽ አጽድቋል።
ነገርግን ሀማስን ከምድረ ገጽ ካላጠፋሁ አላርፍም የምትለው እስራኤል በተመድ ውሳኔ እንደማትገዛ እና ተኩስም እንደማታቆም ገልጻለች።
ሀማስ ተኩስ እንዲቆም እንደሚፈልግ እና ያገታቸውንም ሰዎች እንደሚለቅ ሲገልጽ ቆይቷል።
እስራኤል ተኩስ ለማቆም ፍቃደኛ አለመሆኗን ተከትሎ ሀማስ በሙሉ አቅሙ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።