እስራኤል የሀማስን የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህን መግደሏን አመነች
ስለግድያው በሚስጥር ከእስራኤል መረጃው የደረሳት አሜሪካ በድርጊቱ መቆጣቷ ተሰምቷል
የሀማስ ፖለቲካ መሪ ሀኒየህ መገደሉን ተከትሎ ሀማስ በምትኩ ያህያ ሲንዋርን መሾሙን አስታውቋል
እስራኤል የሀማስን የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህን መግደሏን አመነች
ለሳምን በግድያው ዙርያ በይፋ ሀላፊነቱን ከመውሰድ ተቆጥባ የሰነበተችው ቴልአቪቭ ሀኒየህን ስለመግደሏ በሚስጥር ለአሜሪካ ስለማሳወቋ ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የነጩ ቤት መንግስት ሰዎች በግድያው ዙርያ ከእስራኤል በደረሳቸው መረጃ መሰረት በድርጊቱ መደንገጣቸውን እና መቆጣታቸውን ጋዜጣው ጨምሮ ዘግቧል፡፡
ግድያው አሜሪካ የጋዛውን ጦርነት ለማስቆም በሀማስ እና እስራኤል መካከል የምታደርገውን ጥረት ወደኋላ ይጎትታል ያሉት የነጩ ቤት ሰዎች በእስራኤል ላይ መቆጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ግድያውን ተከትሎ በስልክ ያደረጉት ንግግር በውጥረት የተሞላ እንደነበር ዋሽግተን ፖስት ከምንጮቹ ያገኝው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህ የተነሳም በርካታ የጆ ባይደን አስተዳደር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎች ልክ እንደ ኢራን ሁሉ ኔታንያሁን በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ስጋትነት ፈርጀዋቸዋል ነው የተባለው፡፡
ሆኖም እስካሁን ድረስ ዋሽንግተን ቀጠናዊ ግጭትን ከሚቀሰቀሱ ጠብ አጫሪ ድርጊቶች እስራኤል እንድትታቀብ ጫና ማሳደር አልጀመርችም፡፡
ይልቁንም በእስራኤል ላይ ከኢራን ሊሰነዘር የሚችለውን ጥቃት ለመመከት የጦር መርከቦቿን ወደ ቀጠናው ልካለች፡፡
የሀኒየህ ሞት በተሰማ በሰአታት ውስጥ መረጃው የደረሳት አሜሪካ በአፋጣኝ ባወጣችው መግለጫ ከሀኒየህ ሞት ጋር በተያያዘ እጇ እንደሌለበት አስታውቃለች፡፡
ሀኒየህ በፈረንጆቹ 2021 ላይ በተካሄደ ምርጫ የሀማስ የፖለቲካ ቢሮ መሪ ተደርገው የተመረጡ ሲሆን እስከ 2025 ድረስ በሀላፊነት እንደሚቆዩ ይጠበቅ ነበር፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት በኢራን መዲና ተሄራን ባረፉበት ቤት ውስጥ በፖለቲካ ቢሮ መሪው ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሀኒየህ ከተገደለ ከሰአታት በኋላ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪው የተገደለበት ሂዝቦላ በበኩሉ በእስራኤል ላይ የድሮን እና እና ሮኬት ጥቃት መፈጸም የጀመረ ሲሆን በቀጣይ ከሌሎች አካላት ጋር እና ለብቻ የሚሰጠውን የአጻፋ ምላሽ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዝቷል፡፡
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሀማስ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ያልተጠበቀ ጥቃት ከሀሳብ ማመንጨት ጀምሮ ጥቃቱን እንደመራ የሚታመነው ያህያ ሲንዋር አዲሱ የሐማስ መሪ ተደርጎ ተመርጧል።
እስራኤል የሐማስ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ በሚል በተለያዩ ግንባሮች ዘመቻዋን እንደቀጠለች ሲሆን የአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲአይኤ ቴልአቪቭ ከ30-35 በመቶ ያህል ታጣቂዎችን ብቻ ገድላለች ብሏል፡፡