የቀድሞው የቡድኑ መሪ ካሊደ ማሻል እና የሃኒየህ የቅርብ ሰው ካሊል አል ሀያ ሰፊ ግምት ተሰጥቷቸዋል
የፍልስጤሙ ሃማስ በእስራኤል ለተገደሉበት መሪው ኢስማኤል ሃኒየህ ተተኪ እየፈለገ ነው።
በቀጥታ የሃኒየህ ተተኪ ይሆኑ የነበሩት ምክትላቸው ሳሌህ አሩሪ በጥር ወር በሊባኖስ መዲና ቤሩት መገደላቸው ይታወሳል።
60 አባላት ያሉት የሃማስ ሹራ ምክርቤት በዛሬው እለት የሃኒየህ ግብአተ መሬት በዶሃ እንደተፈፀመ ስብሰባ አድርጎ አዲሱን የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊ ይመርጣል ተብሏል።
አብዛኞቹ የምክርቤቱ አባላት በጋዛ የሚገኙ በመሆናቸውም ሁሉንም አባላት ያሳተፈ ስብሰብ እስኪካሄድ ድረስ የሃኒየህ ተተኪ ዛሬ ወይንም ነገ እንደሚመረጥ አሶሼትድ ፕረስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሃኒየህ ተተኪ ሊሆኑ የሚችሉት እነማን ናቸው?
1. ዛኸር ጃባሪን
የሃማስ ዋና ስራ አስፈፃሚ እየባሉ የሚጠሩት ዛኸር ጃባሪን፥ የቡድኑ የፋይናንስ ጉዳዬች ቁልፍ ሰው ናቸው። ጃባሪን የሃማስን ወጪና ገቢ በመቆጣጠርና በመደልደል ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸው ይነገርላቸዋል። ከኢራን እና ሌሎች ደጋፊ ሀገራት ጋርም ጥሩ ግንኙነት መስርተዋል።
2. ካሊድ ማሻል
የቀድሞው የሃማስ የፖለቲካ መሪ እና የሃኒየህ ምክትል ካሊድ ማሻል የካበተ የፓለቲካና ዲፕሎማሲ ልምድ አላቸው። ይሁን እንጂ ለ2011ዱ የአረብ አብዮት ድጋፍ ከሰጡ በኋላ ከኢራን፣ ሶሪያና ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ግንኙነታቸው ሻክሯል። በ2021 ወደ ቤሩት ባመሩበት ወቅትም የሄዝቦላህ አመራሮች ሊያገኟቸው አልፈለጉም።
ይሁን እንጂ ማሻል ከቱርክ እና የሀማስ የፓለቲካ ቢሮ ከሚገኝባት ኳታር ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ሃኒየህ እንደተገደለ ሀዘናቸውን ለመግለፅ የደወሉት ወደ ካሊድ ማሻል ነው።
3. ካሊል አል ሀያ
ከኢስማኤል ሃኒየህ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አል ሀያ በሃማስ ውስጥ ተሰሚ ናቸው ከሚባሉት ፖለቲከኞች መካከል ግንባር ቀደሙ ናቸው።
በጋዛ የሃማስ መሪው ያህያ ሲንዋር ምክትል ሆነው የሚያገለግሉት ካሊል አል ሀያ ከሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸው። ከኢራን፣ ኳታር፣ ግብፅ እና ቱርክ ጋር ያላቸው ግንኙነትም የሃኒየህ ተተኪ የመሆን እድላቸውን ያሰፋዋል ነው የተባለው።
የሃኒየህን ግድያ ተከትሎ መግለጫ በመስጠት ቀዳሚ የሆኑት አል ሀያ፥ ከእስራኤል ጋር ያለን አማራጭ ትግል ብቻ ነው ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ሃማስ በሶሪያ ጦርነት የፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ተቃዋሚዎችን መደገፉን ተከትሎ የሻከረውን ግንኙነት ለማደስ በ2022 ወደ ደማስቆ የተጓዘውን የሃማስ ልኡክ የመሩትም አል ሀያ ናቸው።
የጋዛ የሃማስ መሪ ምርጫ ሲካሄድ ያህያ ሲንዋርን የተቀናቀኑት ኒዛር አቡ ረመዳን እና ሙሳ አቡ ማርዙቅ (የካሊድ ማሻል ምክትል) የሃኒየህ ተተኪ እንደሚሆኑ ከሚገመቱ የሃማስ አመራሮች መካከል ተጠቅሰዋል።
የሃማስ አዲሱ መሪ የፍልስጤምን ነፃነት በወታደራዊ መንገድ ማረጋገጥ አልያም የተጀመሩ የተኩስ አቁም ድርድሮችን ማስቀጠል አማራጭ ይኖረዋል።
የሃኒየህ ግድያ የፈጠረው ቁጣ ከኔታንያሁ አስተዳደር ጦርነቱን የማስቀጠል ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የሚመረጠው አዲሰ መሪም ለዘብተኛ አቋም ይይዛል ተብሎ አይጠበቅም።