ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀናብሯል የተባለው ሲንዋር በሀኒየህ ምትክ ተሾሟል
ሀማስ በተገደለበት የፖለቲካ መሪ ሀኒየህ ምትክ አዲስ መሪ ሾሟል።
የሀማስ የጋዛ አስተዳዳሪ የሆነውን ያህያ ሲንዋርን ባለፈው ሳምንት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በተገደለው የቀድሞው የሀማስ የፖለቲካ መሪ እስማኤል ሀኒየህ ምትክ መሾሙን ቡድኑ በትናንትናው እለት አስታውቋል።
በአስርት አመታት ውስጥ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን አውዳሚው ጥቃት በዋናነት አቀነባብሯል የተባለው ሲንዋር፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ጋዛ ውስጥ በመደበቅ ከእስራኤል የግድያ ሙከራዎች ማምለጥ ችሏል።
"እስራኤል የጋዛ ጦርነትን ለመቋጨት ከሲንዋር ጋር መነጋገር ይኖርባታል ማለት ነው" ሲሉ በግብጽ እና ኳታር አማካኝነት እየተካሄደ ላለው ድርድር ቅርበት ያላቸው የመካከለኛው ምስራቅ ዲፕሎማት ለሮይተርስ ተናግረዋል።
"ይህ የጥንካሬ እና ያለመበገር ማሳያ ነው" ብለዋል ዲፕሎማቱ።
የወጣትነት ዘመኑን በእስራኤል እስር ቤት ያሳለፈው ሲንዋር፣ በቴህራን ከተገደለው ሀኒየህ ቀጥሎ በህይወት ያለ ከፍተኛ የሀማስ ባለስልጣን ነው። ኢራን ለሀኒየህ ግድያ የበቀል እርምጃ አወስዳለሁ ማለቷን ተከትሎ ቀጣናዊ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
እስራኤል ለሀኒየህ ግድያ ኃላፊነት አልወሰደችም። ነገርገን የሀማስን ምክትል መሪ ሳልህ አል-አሮውሪን እና የቡድኑን ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ ሞሀመድ ዴይፍን ጨምሮ በርካታ የቡድኑን ከፍተኛ አመራሮች ከዚህ በፊት መግደሏን ይፋ አድርጋለች።
በካን ዩኒስ በሚገኘው የስደተኞች ካምፕ የተወለደው የ61 አመቱ ሲንዋር ፍልስጤማውያንን በማስተባበር እና ለእስራኤል ባለው መራር ጥላቻ እውቅና በማግኘቱ በፈረንጆቹ 2017 የሀማስ የጋዛ አስተዳዳሪ ለመሆን በቅቷል።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔኤል ሀጋሪ ሲንዋርን ለጥቅምቱ ጥቃት ተጠያቂ አድርገዋል፤ እስራኤል ትቀጣዋለች ሲሉም ተናግረዋል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎችን ሲገድል፣ ሌሎች 250 ሰዎችን ደግሞ አግቶ ወስዷል። እስራኤል በምላሹ እያካሄደች ባለው መጠነሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት እስካሁን ከ40ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል።