በእስራኤል-ሄዝቦላህ ግጭት፤ ቤሩትና ሌሎች የሊባኖስ ከተሞች በምን ሁኔታ ውስጥ ናቸው?
በ24 ሰዓታት ብቻ በእስራኤል የአየር ድብደባ 35 ህጻትን ጨምሮ 500 ገደማ ሰዎች ተገድዋል
የሊባኖሱ ሄዞቦላህ ወደ እስራኤል በደርዘን የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ተኩሶ ጉዳት አድርሷል
በእስራኤል እና በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሄዝቦላህ ቡድን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት እያገረገሸ እና መጠነ ሰፊ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
የጋዛው የእስራኤልና የሃማስ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ወደ ግጭት ያመሩት እስራኤል እና ሄዝቦላህ አልፎ አልፎ ጥቃቶችን ሲሰናዘወሩ የቆዩ ቢሆንም፤ ካሳለፍነው ሳምንት ወዲህ ግን ወደ ተካረረ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በ24 ሰዓታት ብቻ በሊባኖስ ውስጥ በሚገኙ በ1 ሺህ 300 የሄዝቦላህ ኢላማዎች ላይ ከ650 በላይ ጥቃቶችን መሰንዘሯን አስታውቃለች።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በትናንቱ የእስራኤል ጥቃት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 35 ህጻትን ጨምሮ 492 ሰዎች መሞታቸውን እና 1 ሺህ 645 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል።
ሄዝቦላህም ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፉን የቀጠለ ሲሆን፤ እስራኤል በዛሬው እለት ብቻ ከ50 በላይ ሮኬቶች ተተኩሰውብኛል ብላለች።
እስራኤል የተተኮሱባትን ሮኬቶች አየር ላይ አክሽፊያለው ብትልም፤ ሄዝቦላህ ደግሞ ራሞት ናፍታሊ ወታራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
የእስራኤል ጥቃት በመላው ሊባኖስ ከፍተኛ ስጋትን እና ውጥረትን የፈጠረ ሲሆን፤ በደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ በርካቶችም መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት በቴሌቪዥን በተሰራጨ መግለጫ ላይ፤ “እኛ ችግርራችን ከሄዝቦላህ ጋር ነው ያሉ ሲሆን፤ ሊባኖሳውያን ግጭት ካለበት አካባቢ ራሳቸውን እንዲያርቁ አሳስበዋል።
እስራኤል-ሄዝቦላህ ግጭት ሰለባ የሆኑት አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
እስራኤል ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመችበት ካለው አካባቢ ውስጥ ደቡብ እና ምስራቅ ሊባኖስ ዋነኛው ሲሆን፤ በደቡባዊ ቤሩት፣ ቢንት ጀቢል፣ ሃሪስ፣ ባልቤክ፣ ካፋር ሃታ፣ አረብ ሳሊም፣ ታራያ፣ ሁላ፣ ቶውራ እና ሌሎችም አካባቢዎች ይገኙበታል።
እስራኤል ባሳለፍነው ሳምንት በሊባኖስ ዋና ከተማ በሆነችው ደቡባዊ ቤሩት ላይ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የሂዝቦላህ ወታራዊ አዛዥ ኢብራሂም አቂልን መግደሏ ይታወሳል።