ሊባኖስ በእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 492 ሰዎች ተገድለዋል አለች
በእስራኤል እና በሊባኖሱ ሄዝቦላ መካከል የድንበር ግጭት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወዲህ ይህ ጥቃት እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ነው ተብሏል
የእስራኤል አየር ኃይል በደቡብ ሊባኖስ እና በቤቃ ሸለቆ የሚገኙ 1600 የሄዝቦላ ኢላማውቸን መምታቱን ጦሩ አክሎ ገልጿል
ሊባኖስ በእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 492 ሰዎች ተገድለዋል አለች።
እስራኤል በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላ ይዞታዎችን መምታቷን በገለጸችበት የትናንቱ ጥቃት ቢያንስ 492 ሰዎች መገደላቸውን እና በ10ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለደህንነታቸው ፈርተው መሸሻቸውን የሊባኖስ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
በእስራኤል እና በሊባኖሱ ሄዝቦላ መካከል የድንበር ግጭት ከተጀመረበት ከባለፈው ጥቅምት ወዲህ ይህ ጥቃት እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ነው ተብሏል።
እስራኤል ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት ሄዝቦላ መሳሪያ አከማችቶበታል ካለቻቸው አካባቢዎች ነዋሪዎች እንዲወጡ አስጠንቅቃለች ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለሊባኖስ ህዝብ አጭር የቪዲዮ መልእክት አስተላልፈዋል።
"እስራኤል እየተዋጋች ያለችው ከሄዝቦላ ጋር ነው፣ ከእናንተ ጋር አይደለም። ሄዝቦላ ለረጅም ጊዜ እናንተም እንደሰብአዊ ጋሻ ሲጠቀምባችሁ ቆይቷል" ብለዋል ኔታንያሁ።
ከደቡባዊ ሊባኖስ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቤተሰቦች እቃዎቻቸውን ጭነው ለመሸሽ ተገደዋል።
ለቀውሱ የሚሰጠውን ምላሽ የሚያስተባብረው የሊባኖሱ ሚኒስትር ናስር ያሲን 26ሺ ሰው የመያዝ አቅም ያላቸው 89 መጠለያዎች በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ተቋማት መሰራታቸውን ተናግረዋል።
እስራኤል በደቡባዊ ድንበሯ በኩል ከፍልስጥሙ ሀማስፈ ጋር ለአንድ አመት የቆየ ጦርነት ካካሄደች በኋላ አሁን ትኩረቷን በሊባኖስ በሚንቀሳቀሰው እና በኢራን በማደገፈው ሄዝቦላ ላይ አድርጋለች።
የእስራኤል ጦር እንደገለጸው በደቡብ፣ በምስራቅ እና በሰሜን በሚገኙ የሄዝቦላ "ማስወንጨፊያዎች፣ ማዘዣ ጣቢያዎች እና የሽብርተኛ መሰረተልማቶች" ላይ ጥቃት ፈጽማለች።
የእስራኤል አየር ኃይል በደቡብ ሊባኖስ እና በቤቃ ሸለቆ የሚገኙ 1600 የሄዝቦላ ኢላማውቸን መምታቱን ጦሩ አክሎ ገልጿል።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው 35 ህጻናትን ጨምሮ 592 ሰዎች ሲገደሉ እና ሌሎች 1645 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። አንድ የሊባኖስ ባለስልጣን እንደተናገሩት ይህ የሞት መጠን ከ1975-1990 ከተካሄደ የእርስበእርስ ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ የሚባል ነው።
ጦርነቱ የእስራኤል አጋር የሆነችውን አሜሪካን እና ኢራን ወደ ጦርነት ሊያስገባቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ሁኔታው እንደሚያሳስባት የገለጸችው ሳኡዲ አረቢያ ሁለቱም አካላት ግጭቱን ከማባባስ እንዳቆጠቡ አሳስባለች። አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባልደረባ አሜሪካ የእስራኤል-ሄዝቦላ የድንበር ግጭት እንዲባባስ አትፈልግም ብለዋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት በሄዝቦላ ላይ ከፍተኛ ድብደባ እያደረሱ ያሉት ሄዝቦላ ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲስማማ ለማድረግ መሆኑን እየተናገሩ ናቸው።