የእስራኤል ወታደሮች በራማላህ የሚገኘውን የአልጀዚራ ቢሮ በረበሩ
የኳታሩ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዌስትባንክ ቢሮውን በ45 ቀናት ውስጥ እንዲዘጋ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል
እስራኤል የብሄራዊ ደህንነቴ ስጋት ነው ያለችውን አልጀዚራ በግንቦት ወር በሀገሪቱ እንዳይሰራ ማገዷ ይታወሳል
የእስራኤል ወታደሮች በዌስትባንክ የሚገኘውን የአልጀዚራ ቢሮ በረበሩ።
ጭምብል ያደረጉና የታጠቁ ወታደሮች በቀጥታ ስርጭት ላይ በነበረው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቢሮ ውስጥ ገብተው ፍተሻ ሲያደርጉ ታይተዋል።
ወታደሮቹ ቢሮው በ45 ቀናት ውስጥ እንዲዘጋ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለቢሮው ሃላፊ ዋሊድ አል ኦማሪ ሰጥተውም በቀጥታ መነበቡን ሬውተርስ ዘግቧል።
በራማላህ የሚገኘው የአልጀዚራ ቢሮ ሰራተኞች በ5 ደቂቃ ውስጥ ምንም አይነት እቃ ይዘው ሳይወጡ ከቢሮው እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው በርካታ ወታደሮች ወደ ቢሮ እና ስቱዲዮ ሲገቡና ፍተሻ ሲያደርጉ የሚያሳይ ምስል በቀጥታ ያሰራጨ ሲሆን፥ በ45 ቀናት እንዲዘጋ የተላለፈውን ውሳኔ ተቃውሟል።
የራማላህ የአልጀዚራ ቢሮ ሃላፊው ዋሊድ አል ኦማሪ እንዳሉት የእስራኤል ጦር ቢሮው እንዲዘጋ ውሳኔ ያሳለፈው አልጀዚራን “ሽብርተኝነትን በማነሳሳት እና መደገፍ” በመክሰሱ ነው።
“እስራኤል ወታደሮቿን ወደ ቢሮ በመላክ ጋዜጠኞች ላይ መሰል ድርጊት የፈጸመችው እውነትን ለመደበቅና ለማጥፋት ነው” ሲሉም አጥብቀው ተቃውመውታል።
የጋዛ የሚዲያ ቢሮ ባወጣው መግለጫም የእስራኤልን ውሳኔ እና የቢሮ ወረራ “ሁሉም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾ ይህን የፕረስ እና ሚዲያ ነጻነት ጥሰት ሊያወግዙት” ይገባል ብሏል።
አልጀዚራ በራማላህ ለከፈተው ቢሮ ፈቃድ ያገኘው የፍልስጤም አስተዳደር መሆኑን የሚጠቅሱ የፍልስጤም ባለስልጣናትም እስራኤል የቴሌቪዥን ጣቢያው ስራ እንዲያቆም ማዘዝ እንደማትችል ተናግረዋል።
የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባሉ ኢዛት አል ሪሸቅ በበኩላቸው እስራኤል የአልጀዚራ የራማላህ ቢሮው እንዲዘጋ የወሰነችው የቴሌቪዥን ጣቢያው “እስራኤል በሃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ይዞታዎች የምታደርሰውን በደል ስለሚያጋልጥ ነው” ብለዋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ከ170 በላይ ጋዜጠኞች ተገድለዋል። እስራኤል አለማቀፍ ጋዜጠኞች በገለልተኝነት ለጦርነቱ ሽፋን እንዳይሰጡ ከልክላለች የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳም ይቀርብባታል።
በጋዛ እና ዌስትባንክ ጋዜጠኞችን አሰማርቶ በየእለቱ መረጃዎችን ሲያደርስ የቆየው አልጀዚራ ባለፈው ግንቦት ወር በእስራኤል ውስጥ እንዳይሰራ መታገዱ ይታወሳል።