ቱርክ ለእስራኤል ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸው ሰዎች ላይ በድምር የ250 ዓመት የእስር ቅጣት አሳለፈች
የእስር ቅጣቱ የተከለከለ መረጃ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል የተከሰሱ 37 ሰዎች ተላልፎባቸዋል
ግለሰቦቹ ለእስራኤሉ የስለላ ድርጅት “ሞሳድ” ሲሰልሉ ነበር ተብሏል
የቱርክ ፍርድ ቤት ለእስራኤል ሲሰልሉ ተይዘዋል በተባሉ ሰዎች ላይ በድምር በ250 ዓመት እሰራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳለፈ።
የእስር ቅጣቱ በ37 ሰዎች ላይ የተፈረደ ሲሆን፤ ግለሰቦቹ ለእስራኤል የስለላ ተቋም “ሞሳድ” ሲሰልሉ ተገኝተዋል በሚል ነው ጥፋተኛ ተብለው ፍርዱ የተላለፈባቸው።
ፍርዱ የተላለፈው ቱርክ በጋዛው ጦርነት ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነቷ መቀዛቀዙን ተከትሎ በሞሳድ ወኪሎች ላይ አነጣጥራ እየሰራች በለበት ወቅት ነው።
ለሞሳድ በመሰለል ከተከሰሱት መካከል አህመት ኮራ ኦዝጉሩን እና አልፐረን ኤርቱክ የተባሉት “የተከለከለ መረጃ ለሞሳድ አሳልፈው ሰጥተዋል” በሚል እያንዳንዳቸው በ8 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል።
ቀሪዎቹ 35 ሰዎች ደግሞ በተመሳሳይ ክስ እያንዳንዳቸው የ6 ዓመት ከ8 ወር የእስር ቅጣት እንደተላለፈባቸው ተነግሯል።
ተከሳሾቹ ምን አይነት መረጃ አሳልፈው እንደሰጡ በግልጽ ባይቀመጥም፤ አሳልፈው በሰጡት መረጃ ወሳኝነት ደረጃ የእስር ቅጣቱ እንደተላለፈባቸው ግን ተነግሯል።
የተፈረደባቸው ሰዎች በድምር ወደ 250 የሚጠጉ ዓመታት በእስር ቤት ውስጥ ያሳልፋሉ የተባለ ሲሆን፤ ይህም ቱርክ በሚሳድ ሰላዮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ መጀመሯን ያመላክታል ተብሏል።
ቱርክ ባሳለፍነው ወር በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሞሳድ ዋና ገንዘብ ምንጭ በቁጥጥር ስር እንዳዋለች መነገሩ ይታወሳል።
ቱርክ ከሞሳድ እና ከሌሎች ሀገራት የስለላ ድርጅት ጋር የሚሰሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከዚህ ቀደም የተለያዩ ኦፕሬሽኖችንም አድርጋለች።
ባሳለፍነው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በስምንት ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ 53 ስፍራዎች ባደረገችው አሰሳ ለሞሳድ ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን 33 ሰዎች በቁጥጥር ስር አውላለች።