ከእስራኤል ጋር የተፋጠጠችው ኢራን አዲስ የሰራቻቸውን ሚሳይል እና ድሮን ይፋ አደረገች
ጥጥር ነዳጅ የሚጠቀመው ጂሀድ ሚሳይል እስከ 1000 ኪሎሜትር እንደሚወነጨፍ ዘገባው ጠቅሷል
የኢራኑ ፕሬዝደንት ፔዝሽኪያኒ ከሙስሊም ሀገራት ጥምረት በመፍጠር ዘር አጥፊ ያሏትን እስራኤልን ልክ እንደሚያስገቡ ዝተዋል
ከእስራኤል ጋር የተፋጠጠችው ኢራን አዲስ የሰራቻቸውን ሚሳይል እና ድሮን ይፋ አደረገች።
ቀጣናዊ ውጥረቱ እና ኢራን ሩሲያን እያስታጠቀች ነው የሚለው ክስ እያየለ ባለበት በዚህ ወቅት ኢራን አዲስ ባለስቲክ ሚሳይል እና ድሮን ዛሬ በተካሄደው ወታደራዊ ትርኢት ላይ ይፋ ማድረጓን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ኢራን ሩሲያ በዩክሬን ለምታደርገው ውጊያ ጥቅም ላይ የሚውሉ ድሮኖች እና ሚሳይሎች አስተላልፋ ሰጥታለች የሚለውን የምዕራባውያን ክስ በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ጥጥር ነዳጅ የሚጠቀመው ጂሀድ ሚሳይል ዲዛይኑ የተሰራው እና የተመረተው በኢራኑ ሪቮሉሽናሪ ጋርድ ወይም ጦር የኤሮስፔስ ክፍል ሲሆን 1000 ኪሎሜትር እንደሚወነጨፍ ዘገባው ጠቅሷል።
ሻሄድ-136ቢ የተባለው ድሮን የሻሄድ-136 የተሻሻለ ምርት ሲሆን እስከ 4000 ኪሎሜትር ርቀት ባለው ቦታ ውስጥ መብረር ይችላል ተብሏል።
አዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት መሱድ ፔዝሺኪያን ከ1980-88 ከሳዳም ሁሴኗ ኢራቅ ጋር የተደረገውን ጦርነት ለማስታወስ በተወጋጀው ወታደራዊ ትርኢት ላይ ተገኝተዋል።
"አሁን ላይ የመከላከል አቅማችን በእጅጉ አድጓል፣ ስለዚህ ማንም ኢራንን ስለመውርር አያስብም" ብለዋል ፔዝሽኪያን።
ፕሬዝደንቱ አክለውም "በአንድነት እና ከሙስሊም ሀገራት ጋር ጥምረት በመፍጠር ለሰው ልጆች ምንም ርህራሄ የሌላትን፣ ደም የጠማትን እና ዘር አጥፊዋን እስራኤልን ልክ እናስገባታለን" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ በኢራን እየተካሄደ ባለው አመታዊው የሙስሊም ሀገራት ተወካዮች ጉባኤ ላይ ሙስሊም ሀገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲያቋርጡ እና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን እንዲያዳክሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት የጨመረው በኢራን የሚደገፈው የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነው።
ውጥረቱ ባለፉት ቀናት ውስጥ የተባባሰው እስራኤል ትኩረቷን ወደ ሊባኖስ ድንበር በማዞር፣ በኢራን ይደገፋል ከሚባለው ሄዝቦላ ጋር እየተዋጋች በመሆኑ ነው።
እስራኤል ትናንት ቤሩት ውስጥ በሚገኘው የሄዝቦላ ይዞታ ላይ በፈመችው የአየር ጥቃት ሁለት የቡድኑ አዛዦችን ጨምሮ 31 ሰዎችን ገድላለች።