የእስራኤል ጦር "ውስብስብ በሆነ ዘመቻ" ታጋች ማስለቀቁን ገለጸ
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን አልቃዲን ጠቅሰው እንደዘገቡት ለስምንት ወራት ያህል የጸሀይ ብርሃን አላየም
ጦሩ እንደገለጸው የ52 አመቱ አልቃዲ ከመታገቱ በፊት በጋዛ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ኪቡትዝ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል ነበር
የእስራኤል ጦር ከመሬት ውስጥ በሚገኝ ዋሻ ባደረገው "ውስብስብ በሆነ ዘመቻ" ታጋች ማስለቀቁን ገለጸ።
የእስራኤል ልዩ ኃይሎች ጋዛ በሚገኘው የመሬት ውስጥ ዋሻ ውስብስብ የሆነ ዘመቻ በማካሄድ ለ10 ወራት በታጣቂዎች ተይዞ የነበረን ታጋች ማስለቀቃቸውን የእስራኤል ጦር በትናንትናው አስታወቀ።
ጦሩ እንደገለጸው የተለቀቀው የ52 አመቱ ቃይድ ፋርሃን አልቃዲ የሚባል ሲሆን ከመታገቱ በፊት በጋዛ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ኪቡትዝ የጥበቃ ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል ነበር።
የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኒኤል ሀጋሪ አልቃዲ መለቀቁን ከመናገራቸው ውጭ ዝርዝር መረጃ ይፋ አላደረጉም። የእስራኤል ጦር አልቃዲ የተገኘበት ቦታ ታጋቾች ይገኙበታል ተብሎ ስለሚጠረጠር ውስብስብ የሆነውን የመሬት ውስጥ ዋሻ ኔትዎርክ በርብረዋል።
"ወታደሮቹ ፈረሃንን ሲያገኙት ብቻውን ነበር። ከዚያም ከዋሻው አወጡት" ይላሉ ባለስልጣናቱ። "ይህን ዘመቻ ለማካሄድ ከሌሎች ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ዘመቻዎች ትምህርት ተወስዷል።"
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን አልቃዲን ጠቅሰው እንደዘገቡት ለስምንት ወራት ያህል የጸሀይ ብርሃን አላየም።
አልቃዲን ማናገራቸውን የገለጹት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከእገታ ያስለቀቁትን ወታደሮች አድንቀዋል፤ ሁለም ታጋቾች ተለቀው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እስራኤል ያለማቋረጥ ትሰራለች ብለዋል።
ይህ ዘመቻ እስራኤል በሀማስ ላይ የምታካሂደው ዘመቻ ከተጀመረ ወዲህ ለአንድ አመት ያህል መልካም ዜና ናፍቋቸው በነበሩት የእስራኤል መሪዎች አድናቆትን አግኝቷል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ በከፈተው ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ እና 250 የሚሆኑን ደግሞ አግቶ መውሰዱ ይታወሳል። ከታጋቾቹ ውስጥ በተለያዩ ዙሮች በተካሄዱ ድርድር የተለቀቁ እና የተገደሉ ቢኖሩም አሁንም ከ100 በላይ ታጋቾች በሀማስ እጅ በህይወት አሉ ተብሏል።
እስራኤል የሀማሴን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ እያካሄደችው ባለው ጥቃት እስካሁን ከ40ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።