አፍሪካዊቷ ሀገር ወደ እስራኤል የጦር መሳርያ እያጓጓዘ ነበር የተባለውን መርከብ አገደች
ናሚቢያ የጦር መሳሪያ ጭኗል የተባለ መነሻው ከየት እንደሆነ ያልታወቀ መርከብ ነው አገደች የተባለው
ሀገሪቷ ለፍልስጤም ድጋፏን ለመግለጽ እና በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ያላትን ፍላጎት ለማንጸባረቅ ነው ድርጊቱን የፈጸመችው ተብሏል
አፍሪካዊቷ ሀገር ወደ እስራኤል የጦር መሳርያ እያጓጓዘ ነበር የተባለውን መርከብ አገደች።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናሚቢያ ለእስራኤል የጦር መሳርያዎችን እያጓጓዘ ነበር የተባለን መርከብ ማገዷን አስታወቀች፡፡
መነሻው ከየት እንደሆነ ያልታወቀው መርከብ በውስጡ ተቀጣጣይ ፈንጅዎችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሳርያዎችን ጭኖ በናሚቢያ ወደብ ላይ መልህቁን በጣለበት ነው ጉዞውን እንዳይቀጥል የታገደው፡፡
የናሚቢያ ባለስልጣናት የመርከቡን መነሻ እንደማያውቁ ቢናገሩም ቢቢሲ አገኝሁት ባለው መረጃ መርከቡ መነሻውን ከቬትናም አድርጎ ወደ ሰሜን እየተጓዘ እንዳለ ዋልቪስ ቤይ በተባለ የናሚቢያ ወደብ ላይ ግብአቶችን ለማሟላት በቆመበት እንደታገደ ዘግቧል፡፡
የሀገሪቷ የፍትህ ሚንስትር ይቮን ዳስዋብ መርከቡ ሜድትራንያንን አቋርጦ በጂብራላታር ሰርጥ ወደ እስራኤል እየተጓዘ እንደነበር ደርሰንበታል ነው ያሉት፡፡
ሚንስትሯ አክለውም መርከቡ የጦር መሳርያዎችን ወደ እስራኤል በማጓጓዝ ላይ የነበረ በመሆኑ ናሚቢያ በጋዛው ጦርነት ዙሪያ ባላት አቋም ወደ መዳረሻው እንዳይሄድ እና ቀጣይ የመርከቡ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እመከርንበት ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም እስራኤል በጋዛ እያካሄደች የምትገኝውን ፍትሀዊ ያልሆነ ጦርነት የሚቃወም ማንኛውም አካል ሊወስደው የሚገባውን ውሳኔ ነው ያሳለፍነው ሲሉ ሚንስትሯ ተናግረዋል፡፡
የጋዛውን ጦርነት ከሚቃወሙ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያ ይጠቀሳሉ፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እስራኤልን በዘር ማጥፋት ወንጀል መክሰሷ ይታወሳል፡፡