እስራኤልና ሳኡዲ 2024 ከመጠናቀቁ በፊት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊጀምሩ እንደሚችሉ ተነገረ
የሪፐብሊካኑ ሴናተር ሊንዚ ግርሀም እስራኤልን ከአረቡ አለም ጋር የማስታረቅ ሂደት ከሪያድ ጋር በሚደረግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይጠናከራል ብለዋል
ሳኡዲ ከቴልአቪቭ ጋር ለምትፈጸመው የዲፕሎማሲ እርቅ ከአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሳርያ ሽያጮችን ጨምሮ የመከላከያ ስምምነት ቃል ተገብቶላታል
- እስራኤል እና ሳኡዲ አረብያ ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ የሚደረገው ጥረት የፈረንጆቹ 2024 ከመጠናቀቁ በፊት ሊሳካ እንደሚችል ተገለጸ።
ሪፐብሊካን ሴናተር ሊንዚ ግራሃም ረቡዕ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መነጋገራቸውን እና በእስራኤል እና በሳውዲ አረቢያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማደስ የሚደረገው ሂደት ከዓመቱ መጨረሻ በፊት ውጤታማ እንደሚሆን አምናለሁ ብለዋል፡፡
ለሪፐብሊካን ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በሚቺጋን የሚገኙት ግርሃም ኔታንያሁ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የሚደረገውን ስምምነት እንደሚደግፉ እና ሁኔታዎችን ለማሻሻል ፈቃደኛ መሆናቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ ያስጀመሩትን የአብርሀም ስምምነት የአረቡ አለምን ከእስራኤል ጋር የማሳታረቅ ሂደት ቴል አቪቭ ከሪያድ ጋር በምትጀምረው ግንኙነት ይጸናል ያሉት ሴናተሩ ካማላ ሃሪስ ምርጫውን የሚያሸንፉ ከሆነ የመሳካት እድሉ ጠባብ ነው ብለዋል፡፡
“ባይደን በፕሬዝዳንትነት እያሉ ይህን ማሳካት ይኖርብናል ምክንያቱም ፕሬዝዳንቱ ስምምነቱ እውን እንዲሆን ስለሚፈልጉ አስፈላጊውን የዴሞክራቶችንም ድጋፍ ማሰባሰብ የሚችሉ ይመስለኛል” ነው ያሉት፡፡
በአንጻሩ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የማያሸንፉ ከሆነ እና ካማላ ሃሪስ ስልጣኑን ከያዙ በስምምነቱ ዙርያ ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ በመሆኑ በእርሳቸው ስልጣን ዘመን ስኬታማ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
የሃሪስ ዘመቻ የብሄራዊ ደህንነት ቃል አቀባይ የሆኑት ሞርጋን ፊንኬልስቴይን በበኩላቸው ምክትል ፕሬዝዳንቷ እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ ቀጠና ዘላቂ ውህደት እንዲኖራት የሚደረጉ ጥረቶችን በተከታታይ ደግፈዋል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ያስጀመሩት የአብርሀም ስምምነት ማዕቀፍ በእስራኤል እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በባህሬን፣ በሞሮኮ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻሻል አድርጓል።
ከጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ጋር በተገናኘ በስልጣናቸው መጀመርያ ከሳኡዲ ልዑል አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡት ጆ ባይደን ይህን ስምምነት ማስፈጸም ቢፈልጉም ከሪያድ ጋር በውጥረት ውስጥ የቆየው ግንኙነታቸው ይህን ለማድረግ አላስቻለቻውም፡፡
ከጊዜ በኋላ ከንጉሳዊ አስተዳደሩ ጋር ግንኙነቷን እያሻሻለች የቆየችው ዋሽንግተን፥ ሳኡዲ እና እስራኤልን ለማቀራረብ ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትንም ለማስጀመር ጫፍ ደርሳ የነበረ ቢሆንም የጥቅምት ሰባቱ የሃማስ ጥቃት ሂደቱን እንዳስተጓጎለ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሪያድ ከቴልአቪቭ ጋር ለምትፈጸመው የዲፕሎማሲ እርቅ ከአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሳርያ ሽያጮችን ጨምሮ የመከላከያ ስምምነት ቃል ተገብቶላታል፤ የመከላከያ ስምምነቱ በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን ወይም 67 ድምጽ ያስፈልገዋል።
ከዚህ ባለፈ አብዛኛው እስራኤላውያን የሚቃወሙት ነጻ የሆነች የፍልስጤምን በሀገርነት ለመመስረት የሚያስችል ግልጽ መንገድ ከሌለ እስራኤል እና ሳዑዲ የዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተንታኞች ተናግረዋል።